Tuesday 3 July 2012

በዝምታ መዋሸት?


 ከጓደኞችህ ጋር እያዎራህ/ሽ ነው እንበል። ስለሌላ አንተ ስለምታውቀው ሰው እያወራችሁ ነው። ስለምታወሩት ጉዳይ ጠንቅቀህ ታውቃለህ ነገር ግን መናገር ስላልፈለክ ዝም አልክ። በዝምታህ እያዋሸህ ነው?

 በቅርብ የተዋውቅከው ሰው ወይም እንበል ጓደኛህ በልጅነቱ ስላሳለፈው እና ስላለፈበት ድህነት ያጫውሃል። ስለሚያዎራው ነገር ጠንቅቀህ ታዉቃለህ፣ አንተም ያለፍክበት ስለሆነ። ነገርግን የሚነግርህን በጥሞና አዳምጠህ ስለ ራስህ ሳትነግረው ወሬ ቀየርክ። በዝምታህ እየዋሸህ ነው?

 የምትኖሪው ካገር ውጭ ነው እንበል። ኑሮን ለማሸነፍ የምሰሪውን ስራ ባታፍሪበትም አትኮሪበትም። ስለዚህ አገር ቤት ካሉ ዘመድ ጓደኞችሽ ጋር ስታዎሪ የስራሽን አይነት ሆነ ብለሽ አትጠቅሽም። በዝምታሽ እየዋሸሽ ነው?

 በወንጀል ተጠርጥረህ ፍርድ ቤት ብትቀርብ ወንጀሉን መፈጸም አለመፈጸምህን ስትጠየቅ ዝም ካልክ፣ዝምታህ አልፈጸምኩም እንደማለት ይቆጠርልሃል። ይህ ግምት የሚወሰደው፣ እስኪረጋገጥብህ ድረስ ነፃ ሁነህ የመገመት መብት ስላለህ ነው። በነገራችን ላይ እጅ ከፈንጅ ብትያዝ እንኩዋን ይህን መብትህን አትነጠቅም። ከነጠቁህ ወይም ሲነጠቅ ካየህ በህግ አምላክ ብለህ መጮህ ትችላለህ። የሆነው ሆኖ፣ ወንጀሉን የእውነት ፈጽመህ ቢሆን በህሊና ፍርድ ቤት ሲመዘን በዝምታህ እየዋሸህ ነው?

 በመጨረሻ ይህችን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ “Lying is done with words and also with silence” የሚል አባባል ማንበቤ መሆኑን ሳልገልጽላችሁ ጽሁፌን ብጨርስ ኖሮ በዝምታ መዋሸት ይሆንብኝ ነበር?

No comments:

Post a Comment