Friday 17 August 2012

ምናባዊ ክርክር


ይልቁንም ያይኔን እውነት፣ ለልቤ ያጫወትኩት ቢመስለኝ
ለራሴ የጻፍኩትን ደብዳቤ፣ ላንተ መላኩ አሰኘኝ።
                                                               ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ, ደበበ ሰይፉ, 1966
ምናባዊ ክርክር
ዲሞክራሲ ተኳኩላ ወደ ኢትዮጵያውያን ሄደች- ለሙከራ፤ ብዙዎች አላወቋትም።ይህች ፍቅር የሌላት፣ ክርክር የምታበዛ፣ ባህላችንን የማታከብር፣ በሰው ህመም የምትስቅ፣ በሰው ሞት የምትደንስ፣ ይሉኝታ የሌላት፣ የምንናፍቃት ዲሞክራሲ ወይም የሷ መልእክተኛ ልትሆን አትችልም” ብለው አመሳቀሏት።

 አንዳንዶቹ ግን አውቀዋታል፤ አይተው ግን እንዳላዩ መሆን ፈልገዋል።ይህች ባህላችንን ያልጠበቀች ጋጠ ወጥ ስለሆነች በኛ መካከል ምንም ቦታ የላትም” ብለው እያጥላሏት ነው። ሌሎች ደግሞ እሷ እንደሆነች ቢያውቁም፣ኢትዮጵያዊ መልክ ይዛ ካልመጣች፣ እንዳለ በምእራባዊ ልብስ አጊጣ፣ ተገላልጣ፣ እየጮኸች፣ እያወራች ልትገባ አትችልም” ብለው እየተቃወሟት ነው። 

አንዳንዶች ግንምንም ቢሆን ቦታ ሊሰጣት ይገባል፣ ጉልበተኞችን ማክበር፣ ባለጸጎችን ማክበር፣ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ማለት፣ ገና ለገና ባህላችን ነው ተብሎ እንዴት እንታፈን? እንዴት እንገለል?” እያሉ መጮሃቸውን ቀጥለዋል። ከዛም አልፈው  “ሲጀምር ይህ ባህል የምትሉት የጭቆና መሳሪያ እየሆነ እያገለገለ ስለሆነ መፍረስ አለበት” በማለት በቀጥታ ባይሟገቱም በተዘዋዋሪ ለመታገል እየሞከሩ ነው። ደግሞ ሌሎች አሉ፤እስቲ ቀስ በሉ፤ ሁሉንም ቀስ ብለን ማሳካት እንችላለን፤ ነገሮችን በእርጋታ እና በጥንቃቄ እናድርጋቸው፤ ያልሰራናቸውን የቤት ስራዎች ስለፈለግን ብቻ ከሚጠይቀው ጊዜ በፊት ማጠናቀቅ አንችልም፤ ስለፈለግን ብቻ በረን በሰላም እና በብልጽግና ሜዳ ላይ ማረፍ አንችልም። ህዝባችን ህዝባችን ነውና አፈራችንን አራግፈን አፈር ነህ ልንለው አንችልም። የገባን ነገር ካለ እናስረዳው፤ ከሁሉም በፊት ግን በንቀት ሳይሆን በት ህትና እንረዳው፤ ስሜታችንን በአመክንዮ ለማስደገፍ በምናደርገው ጥረት ጊዜአችንን አናባክን፤”  በማለት በመቅለስለስ ይናገራሉ።

“ምንድነው መለማመጥ?” ሌሎቹ የመልሳሉ።የምትቀሰቅሰው የተኛን ሰው ነው እንጅ አውቆ የተኛ የመሰለን አይደለም፤ የምታስተምረው የማይውቅን ሰው ነው እንጅ አውቆ እውቀቱን በስሜት እና በጠባብነት ይጠቅመኛል ለሚለው አላማ የሚያውለውን ሰው አይደለም። ሃዘኔታ እና ርህራሄ የሚያስፈልገው ደካማው ነው፤ ጥንካሬውን መቆጣጠር አቅቶት ደካሞቹን የሚጨፈልቀው አይደለም፤ብለው በጭሆት ይመልሳሉ።

ተቃራኒው ደግሞ ይከተላል፤እውነት አላችሁ፤ እውነት ግን እናንተ ብቻ አይደለም፤ ልትበሳጩ ትችላላችሁ፣ የሚሰሩ ስህተቶች ሊያሳዝኗችሁ ይችላሉ፤ ነገር ግን ያሳዛኞቻችሁን መሳሪያዎች ልትጠቀሙ አትችሉም። አሳዛኞቻችሁ ጥላቻ ስለተጠቀሙ እናንተ ጥላቻ ልትጠቀሙ አትችሉም፤ አሳዛኞቻችሁ መከፋፈል ስለተጠቀሙ እናንተ መከፋፈል  ልትጠቀሙ አትችሉም። እነሱ ሃያ አራት ሰአት ቢያዎሩ ሃያ አራት ሰአት ችላ ሊባሉ ይችላሉ፤ እናንተ ግን ባገኛችሁት ትንሽ እድል እንደ አሳዳጆቻችሁ ከሆናችሁ ፊት የሚዞርባችሁ ይበዛል።”

መሃል ገብቼ የሆነ ነገር ማለት ፈለኩ፤ ተከራከሩ ድንጋይ ግን አትወራወሩ፤ በሃሳብ ተቧቀሱ ጥይት አለመታኮሳችሁን ግን እንደ ትልቅ ድል ውሰዱት።ካልወደድከኝ አትኖራትም፤ከናቅከኝ አታድራትም” ያባቶቻችን ጨዋታ ነው፤ በቃ በሃሳብ ስለተለያየን፣ ከባህላችን ውጭ የሆነ ነገር ሰለተነጋገርን ኢትዮጵያ አለቀላት ልንል አይገባም፤ ኢትዮጵያ በሽዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በጅማላ ሲገደሉባትም አላለቀላትም፤ እናቶች ለተገደሉ ልጆቻቸው ያላቸውን እንባ አፍነው የጥይት ዋጋ ሲከፍሉም አላለቀላትም፤ አንድ እናት አራት ልጆቿን ምንነቱ ለማይገባት የርእዮተ አለም ልዩነት በአንድ ጀንበር ስታጣም አላለቀላትም፤ ሚሊዎኖች ሆነን በርሃብ ስናልቅ፣ መንግስቶቻችን ችላ ሲሉንም አላለቀላትም። ይህን የምለው አንዳንድ ሰዎች የሚሉትን በቅንነት ከልባቸው እንደሚሉ በመረዳት ነው። ከዚያ ውጭ ግን አውቆ የተኛን ለመቀስቀስ አልፈልግም፤ አልተኛማ።

Thursday 16 August 2012

ይህ አመት ምንድነው?


ይህ አመት ምንድነው?
በ አንጋፋዋ አርቲስት አስናቀች ወርቁ ሞት ይጀምራል፤ ይቀጥልና ሶስት የአገራችንን ሌሎች አንጋፋ ሰዎች ይነጥቀናል፤
ስብሃት ገብረ እግዚያብሄር
ማሞ ውድነህ
ሜትር አርቲስት ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ

የ አገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞቱ ተብሎ አንዳንዶች የፌስ ቡካቸውን መልእክቶች በቁጭት አሸብርቀው፣ አንዳንዶች ሃዘናቸውን በነፍስ ይማር እየገለጹ ትንሽ ቆይቶ፣ 'የለም አልሞቱም' ተባለ፤ እፎይ የሚለው እፎይ አለ፤ ኩምትር የሚለውም ኩምትር አለ። የ ኤርትራው መሪም ኢሳያስ አፈውርቂ ሞቱ ተብሎ አለም አውርቶት፣ "አይ የለም የጠላት ወሬ ነው" ተብሎ የተስተባበለው በዚህ አመት ነበር።

ለኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ጥሩ አመት አልነበረም። ባህር ውስጥ ገብተው አለቁ ይሉናል። http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-18531470

በዚያ አዝነን ሳንጨርስ መኪና ውስጥ ታፍነው ሞቱ ይሉናል። http://africajournalismtheworld.com/2012/06/28/dozens-of-ethiopian-and-somali-refugees-die-in-truck-in-tanzania/
ልባችንን በሃዘን የሰበርውን የሴት እህቶቻችንን የአረብ አገር እንግልት የአለም ደቻሳን ሞት ጨምሮ ማንሳት ይቻላል። አባይ ላይ የተከሰተውን አሰቃቂ የመኪና አደጋ ማስታወስም ይቻላል።

ያም ሆኖ ጉዳችን አላለቀም፤ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንዲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ታመሙ ተባልን፤ አገራችን ባስተናገደችው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ መገኘት አልቻሉም፤ ታዲያ ትንሽም ሳይቆይ አንዳንዶች ሞተዋል ብለው እስከማውራት ደረሱ፤ መንግስታችን "የለም ደህና ናቸው"፤ ይህ የጠላት ወሬ ነው ብሎ ቢያረጋጋንም። እኛን ወሬ ሲፈታን የጋናው ፕረዝዳንት ግን የምር መሞታቸው ተነገረን። በዚሁ አመት የማላዊው ፕሬዝዳንት ሞት መከሰቱን ልብ ይሏል።

በቅርቡ ደግሞ ሌላ የተረጋገጠ መርዶ ደረሰን።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አርፈዋል።

 http://www.danielkibret.com/2012/08/blog-post_7924.html?spref=tw

በዚሁ የኢትዮጵያውን አመት የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ አቡነ ሽኖዳ መሞታቸውን ልብ ይሏል።

ዛሬ ደግሞ ለሁለት ወራት ያነጋገረን የጠቅላይ ሚኒስትራችን የጤና ሁኔታ ወሬ እልባት አገኘ። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አርፈዋል። ነፍስ ይማር!

ይህ አመት ምንድነው- ሞት የነገሰበት? የተሻለ መጭ ጊዜ ለሃገሬ እመኛለሁ።

Tuesday 14 August 2012

መብት ነው ወንጀል?


የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ “አንቀጽ   አላማና ግብ
የወንጀል ህግ አላማ፣ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል አገሪቱን መንግስት፣ የህዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም፣ ደህንነት፣ ስርአት፣ መብትና ጥቅም መጠባቅና ማረጋገጥ ነው።
የወንጀል ህግ ግብ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው።

የዚህን አንቀጽ ትርጉም ለህግ ተማሪዎች ለማስረዳት አንድም ሁለትም ሰአት ሊወስድ የሚችል ቢሆንም እንደምታዩት  ግልጽ እና ህግ ያልተማረም ቢሆን ሊረዳው የሚችል ነው። ማናልባት የኢትዮጵያ ህግ የተቀበለው የቅጣት አላማ መበቀል ነው ወይስ ማረም የሚለውን ጥያቄ ማረም ብሎ እንደሚመልስ ህግ ላልተማረው ግልጽ ላይሆን ይችላል። ማናልባት የህግ ሰው ካልሆንክ በአንቀጹ ውስጥ የተጠቀሱት የቅጣት አላማዎች ሌሎችን ማስተማር(እሱን ያየ ይማር)(general deterrence) ራሱን ወንጀለኛውን ወደፊት ወንጀል እንዳይሰራ ማቀብ(specific deterrence)፣ ጥፋተኛው እንዲማ እና ለህብረተሰቡ ጠቃሚ ሰው እንዲሆን ማድረግ(rehabilitation) እንዲሁም ለተወሰነ ጊዜ ታስሮ በሚቆይበት ጊዜ ሌላ ወንጀል እንዳይሰራ ማድረግ(incapacitation) የሚባሉት መሆናቸውን ለይተህ መተንተን ላትችል ትችላለህ፤ ያም ቢሆን ግን አጠቃላይ ሀሳቡ ግልጽ ነው።

ታዲያ ይህን መልካም አላማ ሰንቆ በተንሳ የወንጀል ህግ አንዳንድ ሰወች ሲከሰሱ እና ሲፈረድባቸው  ለምን ይከፋናል? (እዚህ ከዚህ አስቀድሜ በለጠፍኳት ጽሁፍ ተመስገን ደሳለኝ ተከሰሰ ሲባል አዘንኩ ማለቴን አስታውስልኝ) በህግ የበላይነት ስለማናምን?  ከህጉ ይልቅ ለስሜታችን ስለምናደላ ? ተከሳሹ ወገናችን ስለሆነ?  ለምን ይከፋናል?   ወይስ የወንጀል ህግ ከመንግስት አቃቢ ህጎች እና ከፍርድ ቤቶቻችን ዳኞች ያነሰ ስለሚገባን?  አንዱም አይደለም። አንዳንድ ሰዎችም “ውሳኔው የተሰጠው በፍርድ ቤት ነው”፤ “ይህ የህግ የበላይነት ጉዳይ ነው፤” “ለምን ህግ እንደማታውቁ ትሆናላችሁ?” “አሁን እናንተ ናችሁ ህግን ተማርን እና አስተማርን የምትሉት?”ሊሉን ይችላሉ። እኛ ደግሞ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት ሰውን እንደ እቃ የሚያይ ፍርድ ወስኖ ያውቃል። ማንዴላን ሃያ ሰባት አመት እንዲታሰር የወሰነበት ፍርድ ቤት ነው።  በላይ ዘለቀ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰለን የተገደለው። ከዚያም ሲያልፍ፣ በሂትለር ጊዜ የተፈጸመው ብዙው ነገር ህጋዊ ነበር እንላቸዋለን። "ህጋዊ" የሆነ ነገር ሁሉ ልክ ነው ብለህ ካመንክ መሳሳትክን ከመንገር መዘግየት ያለብኝ አይመስለኝም። የወንጀል ህጉን ተጠቅሞ ፍርድ ቤት ስለወስነ ብቻ እነዚህን ውሳኔዎች ከልባችን ወደን መቀበል አለብን የምትለኝ ከሆነ ልቀበልህ ይከብደኛል። 

እኔ በበኩሌ የወንጀል ህግን የምጠብቀው አብይ ተክለማሪያም እና መስፍን ነጋሽ ላይ ስምንት አመት ፈርዶ እንደነሱ እንዳልጽፍና እንዳልናገር እንዲያስተምረኝ አይደለም። ወይም ደግሞ እስክንድር ነጋን አስራ ስምንት አመት አስሮካደገኛ አስተሳሰቡ” እንዲከላከለኝ አይደለም። አልያም ደግሞ ርእዮት አለሙን አስሮተመስገን ደሳለኝን ከሶ ህብረተሰብን ጎጅ ከሆነየወንጀል ድርጊታቸው እንዲታቀብ እንዲመክርልኝ አይደለም። መንግስት ከዘራፊዎች፣ ከቀማኞች፣ ከነፍሰ ገዳዮች፣ ከሙሰኞች፣ ወዘተ ይጠብቀኝ እንጅ በወረቀት ከሚጽፉ እና በቃል ከሚናገሩ ራሴን መጠበቅ አያቅተኝም/አያስፈልገኝም ።



በማነኛውም መመዘኛ ለሃገሪቱ ጎጂ የማይባሉ ሰዎችን እየወሰደ ማረሚያ ቤት የሚያስቀምጥ የወንጀል ፍትህ ስርአት አስተማሪ ከመሆን ይልቅ ዜጎች በፍርድ ቤቶች ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር ህግን ወደ መሳለቂያነት ሊቀይርብን ይችላል። ወንጀሎችን አቃቢ ህጎች የሚፈበርኳቸው እስኪመስለን ድረስ ባገሪቱ ፍትህ ስርአት ላይ ያለንን መተማመን ያወርድብናል። 
የህግ ባለሙያዎችን ለዚህ ዋነኛ ተባባሪ ናቸው። ስህተትም ቢሆን አንዴ የተወሰደን አቋም በአሳማኝ የህግ ክርክር ለመደገፍ ሁሌም የተዘጋጁ ናቸው። ታዲያ ዳኞቹ እና ተከላካይ ጠበቃዎች ካቃቢ ህጎቹ በተሻለ እና በተደራጀ መንገድ ህጉን እስካልተረዱት ድረስ፣ ፍርድ ቤቱ ነጻም ቢሆን እንኳን በስህተት የተከሰሰውን ሰው ነጻ ሊያደርገው አይችልም። በቅርቡ በርእዮት አለሙ ይግባኝ የታየው የቅጣት መቀነስ ማንልባት ለዚያ ማሳያ ሊሆን ይችላል። 

ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በአንድ የወንጀል ክስ ሂደት ውስጥ ጭብጥ በሚሆንበት ጊዜ፣ ዳኛው "ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ለሌሎች ሰዎች መብትና ክብር(for respect of the rights or reputations of others) እንዲሁም ለአገር ደህንነት እና የህዝብ ደህንነት ብሎም ለህዝብ ጤና እና ሞራል(for the protection of national security or of public order, or of public health or morals) ሲባል ሊገድብ ይችላል" ብቻ ብሎ ማለፍ የለበትም። ሊገደብ ይችላል ማለት ወዲያውኑ ከስምንት እስከ አስራ ስምንት አመት የሚያስቀጣ ወንጀል እስከሚሆን ድረስ ተለጥጦ መታየት የለበትም። ይህንን ሃሳብም ለመረዳት የሚያስችሉ አገራችን በተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ የተመሰረቱ ጥልቅ እና አሳማኝ የህግ ትንታኔዎች አሉ። የአገራችን ዳኞች የነዛን ፈለግ መከተል ትተው "በቃ መገደብ ይችላል! መገድብ ይችላል!" ወደሚል ቀላል መፍትሄ ካዘነበሉ ተከሶ የማይፈረድበት ሰው የሚኖር አይመስለኝም። 

ይህንን ስል በጽሁፍና በንግግር ወንጀል አይፈጸምም እያልኩ አይደለም። ይህንን ስል ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ምንም ገደብ ሊደረግበት አይገባም እያልኩ አይደለም። ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትንም አውሮፓውያን እንኳን ለመቀበል በሚከብዳቸው በአሜሪካውያን የህግ ባህል መሰረት እንረዳው እያልኩ አይደለም።  እያልኩ ያለሁት ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት ስለሆነ ይህ መብት ወደ ወንጀልነት የሚቀየርበት ፍጥነት በጣም ይቀንስ ነው። መብት ነው ስንል ወንጀል ወንጀል ነው ስንል መብት እየሆነ እኮ ተቸገርን። 

  እርግጥ ነው ማንኛውም መንግስት በራሱ ላይ ጦር አንስተው ጦርነት አውጀው የሚዋጉትን ሃይላት እንኳን በወንጀል ህግ በጦር ሃይልም ቢሆን የመዋጋት መብት አለው። ኤርትራ መንግስት ጋር ተባብሮ የኢትዮጵያን መንግስት የሚዋጋ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ በሃገር ክህደት ላይፈረድበት የሚችልበት የህግ ምክንያት ማምጣት ይከብዳል። በዚያ መንገድ የኢትዮጵያን መንግስት የሚታገሉ ሰዎች እራሳቸው ወንጀለኞች ከመሆን አልፈው ሌሎችን በሰላም በሃሳብ እና በቃላት የሚፋለሙ ሰዎችንም ሜዳ እያጠበቡ መሆናቸው ለማንም የሚሰወር አይደለም። ያም ቢሆን ግን ቦንብ በሚወረውሩ ወይም እንዲወረወር በሚያቅዱ ሰዎችን አደባባይ ወጥተው መንግስትን እንዲቃዎሙ እንደሚፈልጉ  በሚጽፉ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት የኢትዮጵያን ህገ መንግስት ከልብ ማንበብ በቂ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ቁጭ ብሎ ብሎግ ላይ ሲጽፍ እና ስብሰባ ላይ ሲናገር የነበረን ሰው በሃገር ክደት ላለመቅጣት እና ሽብርተኛ ላለማለት  አንድ ሽ አንድ ምክንያት መዘርዘር ይቻላል።  የ አረብ አገራት አመጽ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲነሳ እንደሚፈልግ የሚጽፍ ሰው በጣም ሊያናድድህ ይችላል። እኔንም ያናድደኛል። ኢትዮጵያውያን ጎዳና ላይ ወጥተው ንጉሳቸውን የታገሉት ገና በስድሳዎቹ ነበር። ትልቁ የዲሞክራሲ ሙከራችን ከሽፎ፣ የምናስበው ጠፍቶን ምን ማሰብ እንዳለብን በማንስብበት ሰአት ተነሱ እንነሳ ዳንኪራ እኔንም አይመቸኝም። ባይመቸኝም ግን የራሴ ጉዳይ ነው። መንግስት ደግሞ ከኔ በላይ አይመቸውም፤ ባይመቸውም ግን የራሱ ጉዳይ ነው። የማይመችህ በጣም የምትጠላው ንግግር ግን ተናጋሪውን ወንጀለኛ አያደርገውም። በጣም የሚያናድድ ሃሳብ የሚያቀርቡ ሰዎች ቢታሰሩ ኖሮ ኢቲቪ ባዶ ነበር የሚቀረው። 

መብት ሲባል ሌላው ቀርቶ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በአብላጫ ድምጽ(parliamentary majority) እንኳን ሊገፈው የማይችል መሆን አለበት። ነው የብዙሃኑ አገዛዝ፣ አናሳው መብት ማለት። ግለሰብ ደግሞ በጣም ትንሹ አናሳ(the smallest minority) ነው። ከሱ የደከመ፣ ከመንግስት ግዙፍ ጡንቻ በመብት መከለል ያለብት ሌላ ሃይል የለም። 

እባካችሁ የወንጀል ህግን ከዚህ ግርግር አውጡልን።