Wednesday 25 July 2012

በግጥም ስንተክዝ



የኑሮ ጎዳናን ማን መርጦ ይሄዳል

ሲሆን ይወደዳል ባይሆን ይለመዳል

Feb. 11 2012

**********************


ስለ እኔ፣ ስለ እኔ፣ ስለ እኔ አትበሉ
ስለ እናንተ አይደለም መጭው ዘመን ሁሉ፤
መሻገሩ አይቀርም ቢረዝምም ቢበዛም
ይከራያል እንጅ አገር አይገዛም።
       Feb. 12, 2012

*********************

ጥቁር እና ነጭ

ቀለም ነው ያገኘሁ? ቀለሙን ነዉ ያጣው?

እኔ ነኝ የጠቆርኩ? እሱ ነው የገረጣዉ?

ጠይቄ ሳልጨርስ...

ጅምር ጥያቄየን ጥያቄ ረጠው
....
እኛ ከነ ነጮ፣ እኛ ከነ ቡሬ፣ ከነ ወይና አንሰን
ለምን ማሰብ ፈለግን ቀለም ተንተርሰን?

Feb 14, 2012

************************
ህልሙን አስጠብቦ በልኩ እያሰፋ

ካላወቅኩት የለም

ካላየሁት የለም ብሎ እየደነፋ

ተስፋን በመሰለው እየተረጎመ

እዉነትን ባወቀው እየደመደመ
የማይገባኝ ንቋ አይገባም እያለ
እሱ ነው ጠላቴ ተስፋዬን የጣለ
ስለሰፋው ብቻ ህልሜን ያጣጣለ።

Feb 15, 2012

***********************

ሃሳብ ወዳጄ ነው መንገድ ያሳየኛል

በዚህ በዚያ ሂደህ እዚህ ትደርሳለህ ብሎ ይመክረኛል

ዳሩ ይህ ወዳጄ መጥፎ ጠባይ አለው

ደከመኝ አይልም ሳነሳው ስጥለው

ሳባዝት ሳደቀው ስቆርጥ ስቀጥለው።

Feb 16 , 2012

*****************************

ሲቀለኝ በደስታ ሲከብደኝ በሃዘን

አልለካም አለኝ ህይወት አልመዝን

Feb 23, 2012

***************************

አምናዬን ጎትቼ አቆምኩት ከፊቴ

አየሁት በትኩረት ሞገትኩት አብዝቼ

ሂሳቡ ሲሰራ እኔ ሆንኩ ባለ ዕዳ

ግን ደግሞ ተፅናናሁ ...

ካልገባዉ ይሻላል ከርሞ የተረዳ

March 15, 2012

***************************

ከህይወት ባህር ላይ ያሳብ መረብ ጥየ ተስፋን አጠምዳለሁ

የማየውም ባያምር ከማይበት መንገድ ብርታት አገኛለሁ

March 25, 2012

****************************

የታመቁ እንባዎች ጉንጭ የናፈቃቸው
የሽሽት፣ የጭንቀት፣ የክፋት ስር ናቸው።
May 29, 2012


***************************

እንግዲህ ተስፋየን በደመና ጭኜ ላዝንበው ለራሴ

የህይወት በጋዬን የኑሮ ሃሩሬን ቢያርቀው ከነፍሴ
አምናና ዘንድሮን ዘንድሮና ከርሞን አንድ ላይ አስሬ ፊቴ ቁጭ ላርጋቸው
ትዝታም ምኞትም ሃሴትም ጭንቀትም ያሳብ ልጆች ናቸው።

June 17, 2012

No comments:

Post a Comment