Monday 30 July 2012

አዲሱን ፍልሚያ ባሮጌው መንገድ



ነጻነት እኮ ለወዳጆች አያስፈልግም። ዲሞክራሲ እኮ ለደጋፊዎች እምብዛም አያሻም። መንግስት እኮ ለወዳጆቹ ሁሌም ተወዳጅ ነው። ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት በሃሳብ ለሚስማሙህ ሰወች አይደለም በዋነኝነት የሚያስፈልገው። እነሱንማ ፈልገህ ት ሰማቸዋለህ፤ ወደህ ታጨበጭብላቸዋለህ። መብትም ለገዥ ብዙም አትጠቅመውም፤  እርሱማ ፍላጎቱን በጉልበቱ ማስከበር ይችላል።

ዲሞክራሲም የሚያሰፈልገው በፍቅር ለመኖር አይደለም፤ ከልዩነታችን ጋር በሰላም እንድንኖር እንጅ። ነጻነት የሚያሰፈልገው መልካም ቃላትን እንድንለዋወጥ እይደለም፤ መልካም ያልሆኑ ቃላትንም ቢሆን ድንጋይ ሳንወራወር፣ ጥይት ሳንተኳኮስ እንድንደማመጥ እንጅ።

የምንናፍቀው ዲሞክራሲ "ንጉስ" በፍቅር የሚገዛበት አይደለም፤ በፍቅር እንደ አንድ ቤተሰብ የምንኖርበትም አይደለም። የምንናፍቀው ዲሞክራሲ በቃላት የምንፋለምበት፣ ክርክር የሚጦፍበት፣ መሰዳደብ እስኪመስል ድረስ የብዙሃንን ልብ ለማሸነፍ በፖለቲካ የምንተነኳኮስበት ነው። ያ ሁሉ ሲሆን ግነ እንደልጅነታችን በጭዋታው ላይ ማፈር አይቻልም። እንደ በሃላችን "ንቀኸኛል፣ አዋርደኸኛል" ስለዚህ እገድልሃለሁ ማለት አይቻልም። የጠላሃውን ማሰር አትችልም፤ በቃ ክርክሩ ስለሰለቸኝ በጦር መሳሪያ ይዋጣልን ማለት አትችልም።


ስለዚህ ፍቅር ጎደለን ብለህ የምታማርር ከሆነ፣ ለሱ ዲሞክራሲ አይደለም መፍሄው። እንዴት ከባህላችን በወጣ መንገድ ታናግረኛለህ የምትል ከሆነ ለሱም ዲሞክራሲ አይደለም መፍት ሄው። እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በፍቅር እና ባንድነት አገራችንን መገንባት ነው የምንፈልገው ካልክ፣ ለዚያ ዲሞክራሲ ብቻውን የሚበቃ አይመስለኝም። አመለካከታችን አንድ ከሆነማ፣ ምኑን ዲሞክራሲ አስፈለገን ብለህ ነው?

የሃሳብ ልዩነትን እንደ ሃቅ መቀበል ካልቻልን፣ እንዴት አድርገን በጠርጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን ፍጹም በማይገናኙ አመለካከቶች ዙሪያ መከራከር ይቻለናል? አይታችሁ ይሆን በዚህ አመት አንድ ስሜቱን መቆጣጠር ያቃተው የግሪክ አክራሪ ፓርቲ አባል ተከራካሪው ላይ ውሃ ሲደፋ?
  የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሩአዊ መሆኑን ካለመንክ፣ ውስጥህ እያረረም ቢሆን በስርአት መከራከር ካልቻልክ፣ በርግጥ ላንተ የሚሆነው ስርአት ዲሞክራሲ መሆኑን መጠራጠር አለብህ።


የምንናፍቀው ዲሞክራሲ በመሪዎቻችን ላይ የመቀልድ እና የማሾፍ ስልጣን ይሰጠናል። የንጉሱ ወዳጆች ግን ሊመልሱልን እንጅ ሊተኩሱብን አይፈቀድላቸውም። ህግ ሁላችንንም ሊያገለግለን እና ሊመራን እንጅ ለመሪው ብቻ ሊያገለግል አይችልም። መሪዎቻችንም ሊንቀጠቀጡልን እንጅ ሊያንቀጠቅጡን ወደ ስልጣን ላይ አይወጡም።

ነገርግን ዲሞክራሲ ለሁሉም የሚፈልገዉን የሚሰጥ ስርአት አይደለም። ለብዙሃኑ የመምራትን ስልጣን ለአናስው ደግሞ የመብትን ጸጋ ያጎናጽፋል እንጅ። አይ "አንድ ሽህ ሰዎች ተሳስተው አንድ ሰው ብቻ ልክ ሊሆን ይችላል፤ አምሳ አህዮች ቢያናፉ የአንድ መሰንቆ ያህል ጣእም ያለው ዜማ አያወጡም"  ማለት አይቻልም።  እኔ እኮ ተምሬያለሁ፣ ተመራምሪያለሁ፣ የማየው አይታያችሁም፣ የምሰማው አይሰማችሁም ፣ ዝም ብላችሁ ተከተሉኝ ማለት አይፈቀድም።

ታዲይ አንዳንዴ ሳስበው ይህ ይምንናፍቀው ዲሞክራሲ ሊቸረን የማይችለውን ቱሩፋት የምንጠብቅበት ይመስለኛል። ዲሞክራሲ አንድ እንድንሆን አያደርግነም፤ በልዩነታችን ምክንያት በጦር እንዳንፋለም እንጅ። ዲሞክራሲ በፍቅር እንድንኖር አያደርገንም፤ ጠባችንን በሃሳብ እና በድጋፍ ማሰባሰብ እንድንፈታ እንጅ። ለዚህም ነው መቻቻል፣ መከባበር፣ እና አንዱ ሌላውን መርዳት አስፈላጊ እሴቶች የሚሆኑት። ይህንን ከተረዳን እና ካደረግን ተስፋ አልን፤ አለበለዚያ ግን በዲሞክራሲ ስናሸንፍ የተሸነፍን እየመሰለን መቸገራችን እይቀርም። አለበለዚያ ግን ጀግኖቻንን እያሰርን እድሜ ልክ እየፈረድን፣ስህተቱን እኛው ሰርተን ተበዳዩን ይቅርታ እያስጠየቅን፣ አዲሱን ፍልሚያ ባሮጌው መንገድ እየተፋለምን መኖራችን ነው።

በዲሞክራሲ ስርአት ያንተን ህልም ሌሎች ላይ መጫን አትችልም፤ ያንተን አላማ ብታምንበትም ማሳመን ካልቻልክ ዳር ቆመህ መጮህ እንጅ መሃል ገብተህ መንጠቅ አትችልም። ታዲይ ዳር ያሉት ሲጮሁ መሃል ያሉት ወይም ነን የሚሉት አገር ተረበሸ፣ ሽብርተኞች ነገሱ ማለት አይችሉም። የምንናፍቀው በፍቅር የምንኖርበት ሃይማኖታዊ ስርአት አይደለም፤ዲሞክራሲ እንደዚያ ሊሆን አይችልምና። ልዩነታችንን እና ጭሆታችንን እንደ ሙዚቃ ማጣጣም አለብን። ያን ማድረግ ካልቻልን ይህ ስርአት ወይ ይጠበናል ወይ ይሰፋናል ማለት ነው። ወይ አድገን እስክንሞላው፣ ወይ አንሰን እስኪበቃን በማስተዋልና በጥንቃቄ በመረዳትም እንታገል።

No comments:

Post a Comment