Monday 30 June 2014

የታሰሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ጉዳይ ትኩረት ሊነፈገው አይገባም

ትናንትና ከዞን ናይኖች መካከል ሶስቱ ፍርድቤት ቀርበው ፖሊስ ሌላ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ ሁለት ሳምንት ገደማ እንደፈቀደ ሰምተናል። በጸረ ሽብርተኝነት ህጉ እያንዳንዱ የጊዜ ቀጠሮ ከሃያ ስምንት ቀን ማነስ የሌለበት ሆኖ ሳለ( አጠቃላይ የምርመራ ጊዜው ከ አራት ወር እስካልበለጠ ድረስ) አነስ ያለ የጊዜ ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት ጉዳዩ ተመልሶ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት መታየት በመጀመሩ ይሁን ወይም በዳኛው ስ ህተት ወይም ደግሞ ጉዳዩ ከቀሪዎቹ ተከሳሾች ጋር በሁለት ሳምንት በመለያየቱ ያንን ለማስተካከል ከመንግስት በተዘዋዋሪ በመጣ ትእዛዝ ለማወቅ አይቻልም። የሆነው ሆኖ ስለዚህ ጉዳይ ለመጻፍ ሳስብ አንዳንድ የፌስ ቡክ ወዳጆቼ  ከተቃውሞ ሰልፉ ጋር በተያያዘ የታሰሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ይፈቱ የሚል ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነ ተረዳሁ። ዞን ናይኖች እንዲህ በብዙ ሰው ትኩረት ውስጥ ሆነው ሳለ እስካሁን ባለው ሂደት የታዩና የተሰሙ አንዳንድ ሁኔታዎችን ስናስብ፣ በተመሳሳይ የህዝብና የሚዲያ ትኩረት ውስጥ ያልገቡ በየቦታው ከተቃውሞ ሰልፉ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ለመብት ጥሰትና ለእንግልት ከዞን ናይኖችም በላይ የተጋለጡ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። ከዞን ናይኖች ጉዳይ ጋር እያዛመድን አንዳንድ ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን። 

የታሰሩ የኦርሞ ተማሪዎች በተያዙ በ አርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ወይ?
በዞን ናይኖች ክስ ሂደት መንግስት በትክክል ከሰራቸው ነገሮች አንዱ በወንጀል ጠርጥሪያቸዋለሁ ብሎ ከያዛቸው በኋላ በ አርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ማቅረቡ ነበር። ፍርድ ቤት የመቅረባቸው አላማ የሆነው የተያዙበትን ምክንያት በቂነት የማረጋገጥና ከጠበቃና ከዘመድ ተለይተው እንግልት እንዳይደርስባቸው የማድረግ አላማ በሚገባ ተደርጓል ባይባልም፣ ፍርድ ቤት በጊዜው መቅረባቸው ባያስመሰግንም አያስወቅስም። ከተቃውሞ ሰልፉ በኋላ የተያዙ የኦሮሞ ተማሪዎች በእርግጥ የተያዙት በወንጀል ተጠርጥረው ከሆነ  ተመሳሳይ በቶሎ ፍርድ ቤት የማቅረብ ተግባር መፈጸሙን አናውቅም። 

ተማሪዎቹ ከተለያየ አይነት የእንግልት እና የማሰቃየት ተግባር ተጠብቀዋል ወይ? 
የብዙዎቻችንን ትኩረት አግኝቶ የነበረው የዞን ናይኖች ጉዳይ ልጆቹን በ አርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት በማቅረብ ቢጀመርም፣ ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ከቤተሰብና ከጠበቃ ለይቶ በማቆየት የጊዜው መንግስት እንደዚህ ትኩረትን በሚስቡ እና ሰው ሁሉ በሚከታተላቸው ጉዳዮች እንኳን ለ አገሪቱ ህገ መንግስትና መብትን የሚደነግጉ ህጎች ያለውን ንቀት አሳይቷል። ይህ ሁኔታ ትኩረት ባገኘው የዞን ናይኖች ጉዳይ እንዲህ ያለው ተግባር ከተፈጸመ፣ በተለያዩ የ አገሪቱ ክፍሎች በብዛት ለእስራት በበቁትና ቁጥራቸው ተለይቶ በማይታወቅ ወጣቶች ላይ ምን ተደርጎ ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ከዞን ናይን ታሳሪዎች መካከል የተወሰኑት ፍርድ ቤት ቀርበው የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞብናል ሲሉ በተናገሩት ላይ ተመስርቶ የተደረገ የምርመራም ሆነ የማጣራት ተግባር አለመኖሩ የጊዜው መንግስት እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ተግባር ለመከላከልም ሆነ ሲደርስ እርማት ለመውሰድ ተቃማዊም ሆነ የ አሰራር ዝግጁነቱ እንደሌለው ግልጽ አድርጎታል። እንዲህ ትኩረት በሳበ ጉዳይ ላይ እንዲህ ያለው ግዴለሽነትና ማን አለብኝነት  ከተስተዋለ በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች በታሰሩ ተማሪዎች ላይ ይህን የመሳሰለው ነገር እንዳልተፈጸመ ምን ማረጋገጫ ይኖራል? አያያዛቸው ከዞን ናይኖች አያያዝ የባሰ እንደሚሆን ግን መገመት ይቻላል። በፖሊስ ይዞታ ውስጥ ሆኖ የሞተ ተማሪ እንዳለ ሁሉ ሰምተናል። ይህን ተከትሎ ምን ምርመራ ተደረገ? ምናልባትም ምንም። እንደ ሰብ አዊ መብት ኮሚሽን ያሉ ተቋማት ከውጭ የሰብ አዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመሟገት የ አገሪቱን ገጽታ ላለማበላሸት እየጣሩ እንደሆነ ነግረውናል። የቱሪዚም ቢሮ ናቸው እንዴ እነሱ?

አንዳንድ ሰዎች ተጠርጣሪዎች በቀጥታ ፍርድ ቤት እየቀረቡ የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞብናል፣ እንዲህ እና እንዲያ ያለው እንግልት ተደርጎብናል እያሉ እንኳን አንዳች ድንጋጤና ጭንቀት አይሰማቸውም። ለምን እንደሆነ አይገባኝም። በደርግ ጊዜ ያ ሁሉ የማሰቃየት ተግባር በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ሲፈጸም የወቅቱ ስርዓት በንጉሱ ጊዜ የወጡ ተጠርጣሪዎች በተያዙ በአርባ ስምንት ሰዓት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ ተገደው ቃላቸውን እንዳይሰጡ፣ ጠበቃ እንዲያገኛቸው ወዘተ የሚደነግጉ ህጎችን እንደማይጠቅም የፍ ትህ አተያይ ቆጥሮ ችላ ብሏቸው  እንደነበረ ልንረሳው አይገባም። አሁንም በህገ መንግስቱ እና በሌሎች ህጎች ላይ የተቀመጡ የዜጎችን መብቶች በተመለከተ ከርዕዮተ አለማዊ ዝንባሌ የሚመነጭ የንቀት አተያይ በ አንዳንድ ሰዎች ዘንድ አስተውላለሁ። ስለ መብት የሚያወራ ሰው ስለ አገሪቱ መልካም ነገር ማውራት የማይፈልግ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩም አሉ። ይሄ ትክክል አይደለም። ስ ለ አገሩቱ መልካም መልካሙን ብቻ መርጦ ማውራት አገርን መውደድ አይደለም። ደርግም በጣም ለብዙ ዘመናት በሰሜን የነበረውን ጦርነት ከኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ደብቆ እንደኖረ ልናስታውስ ይገባል። ርሃብንም የደበቅንበትና ሰው በጠኔ እንዲሞት የፈቀድንበት ታሪክ አለን። በቀይ ሽብርና ከዚያም በኋላ በ አገሪቱ ውስጥ የሆነውንና የተደረገውን ኢሰብዓዊ ድርጊት በሚገባ አውግዘን እንዳይደገም ለራሳችን ቃል ገብተን እየኖርን አይደለም ያለነው። ይሄ ደግሞ መሻሻሎች ቢኖሩም ከግፍ ቀለበት እንዳንወጣ አድርጎናል። የለመለመ መስክና የተንጣለለ አስፋልት እያሳዩ መመጻደቅ አገርን መውደድ አይደለም። የ አሜሪካ ጦር በኢራቅ አቡግራይብ እስር ቤት የፈጸመውን ግፍ ያጋለጡት እና ያራገቡት እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽና ያሉ የሰብ አዊ መብት ተሟጋቾች ናቸው። ተመሳሳይ ድርጅት የተቃውሞ ሰልፎቹን ተከትሎ እንዳወጣው ያለውን አይነት መግለጫ በትኩረት አይተን እርምጃ ብንወስድ የምንጠቅመው እኛ ነን። የምናሰቃየው፣ የምናዋክበው እና የምናንገላታው እንደ አሜሪካኖቹ እንኳን በሰው አገር ሄደን አይደለም። የገዛ ህዝባችንን ነው። ያንቀላፋ ህሊናችን ሊነቃ ይገባል።  በየ እስር ቤቱ ያሉ የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመባቸውን ማሰቃየት፣ በደልና እንግልት ሊቆም ይገባል። ነጻነታቸውንም ማግኘት አለባቸው። 


Wednesday 21 May 2014

ህግና ፍትህ- በቅርቡ በኦሮምያ የተከሰተው የተቃውሞ ሰልፍ ሂደት በገለልተኛ አካል መመርመር አለበት



ብዙ ሰዎች ህግን ያከብራሉ፤ መንግስታትም ሰዎች ለህግ እና ለህግ ስርዓት በሚሰጡት ክብር ይጠቀማሉ። ህግ ግን የተገቢነት ብቸኛ መለኪያ አይደለም። ምክንያቱም ህግ ጉልበተኞች ደካሞችን የሚጨፈልቁበት የጭቆና መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላልና ነው። ከጥንትም ጀምሮ ብዙ ሰዎች ፍትህ ማለት የተጻፈው ህግ እንዳለ መተግበር ነው ብለው ያስባሉ። ህጉ ቁራሽ ዳቦ እርቦት የሰረቀ ሰው መገደል አለበት ካለ፣ ሰውዬው ይህን ማድረጉ እስከተረጋገጠ ድረስ መገደሉ ፍትሃዊ ነው ይላሉ። ህጉ ንጉሱን የሰደበ መገረፍ አለበት ካለ፣ አጥፊው ንጉሱን መስደቡ እስከተረጋገጠ ድረስ መገረፍ አለበት ይላሉ። ህጉ ሃይማኖት የቀየረ ሰው ተሰቅሎ መገደል አለበት ካለ፣ ይሄንኑ ነገር ማድረግ ፍትሃዊ ነው ይላሉ።

ህግ ራሱ መልሶ የተገቢነት ጥያቄ ይቀርብበታል። ፍትህ ወረቀት ላይ የተጻፈውን ህግ ከመተግበር የዘለለና፣ ህግ ራሱ ተገቢነቱ የሚለካበት ሚዛን ተደርጎ የሚታይበትም ሁኔታ አለ። በተለይ የመንግስት ስልጣን በተቀየረ ጊዜ፣ ወይም አንድ ሃይለኛ ጉልበት የነበረው መንግስት በጦርነት በተሸነፈ ጊዜ ሁሉ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ህጋዊ ተብለው የተፈጸሙ ነገሮች ሁሉ እንደገና በወንጀልነት ይጠየቃሉ። ከሁለተኛው አለም ጦርነት መገባደድ በፊት በናዚ ጀርመን እና በጃፓንም ሃይሎች የተፈጸሙ ወንጀሎች ለፍርድ ቀርበዋል። ከዚያም በኋላ በየጊዜው በተለያዩ አገራት የነበሩ አምባገነኖች የፈጸሟቸው ወንጀሎች ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ለፍርድ ዳኝነት ቀርበዋል። አሁን ህግን ሁሉ እንዳለ መተግበር እንደ ፍትህ የሚቆጠርበት ጊዜ አክትሟል። ከተባበሩት መንግስታት መቋቋም በኋላ የሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሃሳብ ማነኛውንም ህጋዊ ተብሎ የሚፈጸም ተግባር ተገቢነት ለመመዘን የሚያስችል የፍትህ ሚዛን ሆኗል። ዛሬ በአገረ ሱዳን ህግ መሰረት በፍርድ ቤት ሞት የተፈረደባት እርጉዝ ሴት እንዳትገደል አለም የሚጮኸው በዚህ የፍትህ ሚዛን ተለክቶ ህጋዊ የተባለው ነገር ቀሎ ስለሚታይ ነው።

ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን በመቀበል ከአገራት ባትዘገይም፣ ብዙ ጊዜ መብቶቹን ለማክበር የሚያስፈልገው ቁርጠኝነት፣ ተቋማት፣ አስራር እና ባህል እጥረት አንቆ ይይዛታል። ንጉሱ በምዕራባውያን አርቃቂዎች ያሰሯቸው ህጎች የህዝብረተሰቡን ባህልና አኗኗር የሚያንጸባርቁ ባይሆኑም፣ ዜጎችን በተሻለ ክብር ለማስተናገድ የህዝቡንም ባህል በህጎቹ አቅጣጫ ለማስኬድ ጥሩ መነሻ ነበሩ። ደርግ በርዕዮተ አለማዊ ምክንያቶች እነዚያን ህጎች ችላ አላቸው።በወቅቱ ነገሮች ከሚታዩበት ርዕዮተ አለማዊ መነጸር በመነሳት፣ ህጉን ላወጣው ስርዓተ ማህበረሰብ በነበረው ንቀት የተነሳ በህጉ ውስጥ የተካተቱት ጠቃሚ ነጥቦች ተረሱ። አሁን ህገ መንግስታዊ እውቅና ያላቸው ነጻ ሆኖ የመገመት መብት፣ በራስ ላይ እንዲመሰክሩ ያለመገደድ መብት፣ ጠበቃ በተቻለ ፍጥነት የማግኘት መብት ወዘተ በሙሉ በንጉሱ ጊዜ በወጡ ህጎች ውስጥ የተካተቱ ነበሩ። እነዛ ሁሉ ችላ ተብለው ሰዎች ያለ ፍርድ ተገደሉ። ህግን የጨቋኞች መሳሪያ ብለው የሚጠየፉት፣ ያለ ህግ ድጋፍ አብዮታዊ እርምጃን መውሰድ ፍትህ ነው ብለው ወሰዱት።   በደርግ ጊዜ በዋና ዋና የ አገሪቱ ከተሞች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ማሰቃየቶች ሁሉ በተፈጸሙበት ወቅት አብዮታዊ እርምጃዎች ተብለው ቢንቆለጳጰሱም፣ ተጎጅዎቹም ጸረ ህዝቦች ተብለው ስርዓት ያለው ቀብር ቢነፈጉም፣ ጊዜው ሲደርስ እንባቸውን እንዲውጡ የተጠየቁት ሰዎች ዝም ባሰኟቸው አሳሪዎቻቸው ፊት ለመመስከር በቅተዋል።

አሁንም ለህግ ከሚሰጠው ክብር የመንግስትን ቅቡልነት ብቻ ለማግኘት እየተጠቀሙ፣ በእርግጥ ግን ህግን በከፍተኛ ንቀት ማየት አልቆመም። የጊዜው መንግስት ሰዎች ከደርግ ጋር ከተመሳሳይ የርዕዮተ አለም ወንዝ ስለሚቀዱ፣ አሁንም የህገ መንግስቱ የሰብዓዊ መብት አንቀጾች በንቀት ይታያሉ። በተለይ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች የሚባሉት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የባህል መብቶች ከሚባሉት እንዲሁም ከቡድን መብቶች ባነሰ አይን የሚታዩ ይመስላል።

በጊዜው መንግስት የስልጣን ቆይታ በፊት ከነበረው የተሻሻለ ብዙ ነገር እንዳለ ባይካድም፣ አሁንም ቢሆን አገሪቱ አለኝ በምትለው ህገ መንግስትና፣ አጽድቂያቸዋለሁ የህጎቼም አካል ናቸው በምትላቸው አለም አቀፍ ህጎች መሰረት የመንግስትን ስልጣን የመገደብ ጉድለት አለ። ይሄ ጉድለት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች መብቴ የሚለውን ለመጠየቅ ሲሞክር፣ አንዳንዴም ሃይል የቀላቀሉ ሰላማዊ ሰልፎች ሲደረጉ ጎልቶ ይወጣል። በቅርቡ በኦሮምያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ የሆነውም ይሄው ነው። በአለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ህግ መሰረት በአጠቃላይ ሰላማዊ ሰልፎች፣ ሃይል የቀላቀሉም ቢሆኑ እንዴት መስተናገድ እንዳለባቸው የሚዘረዝር አሰራር አለ። በቅርቡ የተካሄዱትን ሰልፎች እና የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ ምን ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ይዘረዝራል። አገር ውስጥም ቢሆን ውስጥ በነዚህ ሁኔታዎች ምን መደረግ እንዳለበት ጠንቅቀው የሚያውቁ ብዙ ባለሙያዎች አሉ።

ባሁኑ ሰዓት ከሁሉም በላይ የሚያስፈልገው ጉዳዩን የሚመረምር እና በተቃውሞ ሰልፍ ሂደቱ የነበረውን የመንግስት የሃይል አጠቃቀም፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ዜጎች ቁጥር፣ ከታሰሩ በኋላ የድብደባ እና የማሰቃየት ተግባራት መፈጸም አለመፈጸሙን ወዘተ በገለልተኝነት መርምሮ ለመንግስትና ለህዝብ የሚያቀርብ ገለልተኛ አካል ነው።የመንግስት ሃይሎች ሃይል ተጠቅመው ህይወት ከጠፋ፣ ነገሩ ስለተፈጸመበት ሁኔታ መልሶ ምርመራ ማድረግና የሃይል አጠቃቀሙ ላይ ችግር ከነበረ ጥፋተኞችን መቅጣት በህይወት የመኖር መብትን የማክበር ግዴታ አካል ተደርጎ የሚታይ አሰራር ነው። የጠፋ ህይወት አይመለስም። ነገርግን ጉዳዩን መርምሮ፣ ስ ህተቶችን ማረም ለወደፊቱ ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር አንድ ሃላፊነት ከሚሰማው ስርዓት የሚጠበቅ ነው። ዝም ብሎ በጭፍን ሁሉንም የፖሊስ አሰራር ልክ ነው ማለት፣ ወይም ሰልፈኞቹን ተጠያቂ ማድረግ ጸረ ሰብዓዊ መብት የሆነ አሰራር ነው።  

 በመሰረቱ ሃይል የቀላቀለ ሰልፍ የማይደረግበት አገር የለም። ከሰብዓዊ መብት አንጻር ጥቅም ላይ መዋል ያለበት መርህ ግን ተመሳሳይ ነው። ከተወሰኑ አመታት በፊት በእንግሊዝ የአንድ ወጣትን በፖሊስ መገደል ተከትሎ የተነሳውን ሁከት ማስታወስ ይቻላል። በተለያዩ ከተማዎች በነበረው ሁከት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ባልሳሳት ከአምስት አይበልጥም። በሂደቱ የታሰሩት ሰዎችም ቁጥር ግልጽ ሆኖ የሚታወቅ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ ማዕቀፉ ቢኖርም እንደዚህ አይነት አሰራሮችን በማስፈን ፋንታ መንግስት በመሰረቱ እስካሁንም የሚሰራው ባረጀ እና ባፈጀ አካሄድ ነው። መርሁም አንድ ይመስላል፤ ፕሮፓጋንዳ ፕሮፓጋንዳ አሁንም ፕሮፓጋንዳ። ከዚህ በፊትም ከቶርቸር ጋር አያይዤ በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ እንደጠቀስኩት፣ እንደዚህ የሚቀጥል ከሆነ ይህም ስርዓት እንደ ደርግ እያሉ ግን ችላ በተባሉ በራሱ ህጎች የሚጠየቅበት ቀን ይመጣል። መንግስት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ሲል፣ ያለው ህገ መንግስት በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ከተቃውሞ ለመከላከል የወጣ ይመስል፣ የዜጎችን መብት የሚዘረዝረው ክፍል ይረሳል። ይህን የብዙ ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበትን የተቃውሞ ሰልፍ ሂደት በገለልተኛ አካል አስመርምሮ ጥፋተኞች ሃላፊነት እንዲወስዱ፣ ተጎጅዎች ካሳ እንዲያገኙ፣ ህዝብም እውነቱን እንዲያውቅ ካላደረገ የሟቾቹን በህይወት የመኖር ሰብዓዊ መብት እንደጣሰ እንደሚቆጠር ሊታወቅ ይገባል።  ሁሉንም የሚጠቅመው አካሄድ ግን ቀላል ነው። ሰብዓዊ መብትን ለማክበር የሚጥርና ስህተት ሲሰራ የሚያርም አሰራር መፍጠር የማይቻል አይደለም። ይሄ ደግሞ አሁን በሂደት ካልተፈጠረ ጉልቻም ቢቀየር እንኳን የወጡ ጣዕም አይቀየረም። መቼም ህዝብ ከሌላ አገር ማስመጣት አይቻልም።