Monday, 30 July 2012

አዲሱን ፍልሚያ ባሮጌው መንገድ



ነጻነት እኮ ለወዳጆች አያስፈልግም። ዲሞክራሲ እኮ ለደጋፊዎች እምብዛም አያሻም። መንግስት እኮ ለወዳጆቹ ሁሌም ተወዳጅ ነው። ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት በሃሳብ ለሚስማሙህ ሰወች አይደለም በዋነኝነት የሚያስፈልገው። እነሱንማ ፈልገህ ት ሰማቸዋለህ፤ ወደህ ታጨበጭብላቸዋለህ። መብትም ለገዥ ብዙም አትጠቅመውም፤  እርሱማ ፍላጎቱን በጉልበቱ ማስከበር ይችላል።

ዲሞክራሲም የሚያሰፈልገው በፍቅር ለመኖር አይደለም፤ ከልዩነታችን ጋር በሰላም እንድንኖር እንጅ። ነጻነት የሚያሰፈልገው መልካም ቃላትን እንድንለዋወጥ እይደለም፤ መልካም ያልሆኑ ቃላትንም ቢሆን ድንጋይ ሳንወራወር፣ ጥይት ሳንተኳኮስ እንድንደማመጥ እንጅ።

የምንናፍቀው ዲሞክራሲ "ንጉስ" በፍቅር የሚገዛበት አይደለም፤ በፍቅር እንደ አንድ ቤተሰብ የምንኖርበትም አይደለም። የምንናፍቀው ዲሞክራሲ በቃላት የምንፋለምበት፣ ክርክር የሚጦፍበት፣ መሰዳደብ እስኪመስል ድረስ የብዙሃንን ልብ ለማሸነፍ በፖለቲካ የምንተነኳኮስበት ነው። ያ ሁሉ ሲሆን ግነ እንደልጅነታችን በጭዋታው ላይ ማፈር አይቻልም። እንደ በሃላችን "ንቀኸኛል፣ አዋርደኸኛል" ስለዚህ እገድልሃለሁ ማለት አይቻልም። የጠላሃውን ማሰር አትችልም፤ በቃ ክርክሩ ስለሰለቸኝ በጦር መሳሪያ ይዋጣልን ማለት አትችልም።


ስለዚህ ፍቅር ጎደለን ብለህ የምታማርር ከሆነ፣ ለሱ ዲሞክራሲ አይደለም መፍሄው። እንዴት ከባህላችን በወጣ መንገድ ታናግረኛለህ የምትል ከሆነ ለሱም ዲሞክራሲ አይደለም መፍት ሄው። እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በፍቅር እና ባንድነት አገራችንን መገንባት ነው የምንፈልገው ካልክ፣ ለዚያ ዲሞክራሲ ብቻውን የሚበቃ አይመስለኝም። አመለካከታችን አንድ ከሆነማ፣ ምኑን ዲሞክራሲ አስፈለገን ብለህ ነው?

የሃሳብ ልዩነትን እንደ ሃቅ መቀበል ካልቻልን፣ እንዴት አድርገን በጠርጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን ፍጹም በማይገናኙ አመለካከቶች ዙሪያ መከራከር ይቻለናል? አይታችሁ ይሆን በዚህ አመት አንድ ስሜቱን መቆጣጠር ያቃተው የግሪክ አክራሪ ፓርቲ አባል ተከራካሪው ላይ ውሃ ሲደፋ?
  የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሩአዊ መሆኑን ካለመንክ፣ ውስጥህ እያረረም ቢሆን በስርአት መከራከር ካልቻልክ፣ በርግጥ ላንተ የሚሆነው ስርአት ዲሞክራሲ መሆኑን መጠራጠር አለብህ።


የምንናፍቀው ዲሞክራሲ በመሪዎቻችን ላይ የመቀልድ እና የማሾፍ ስልጣን ይሰጠናል። የንጉሱ ወዳጆች ግን ሊመልሱልን እንጅ ሊተኩሱብን አይፈቀድላቸውም። ህግ ሁላችንንም ሊያገለግለን እና ሊመራን እንጅ ለመሪው ብቻ ሊያገለግል አይችልም። መሪዎቻችንም ሊንቀጠቀጡልን እንጅ ሊያንቀጠቅጡን ወደ ስልጣን ላይ አይወጡም።

ነገርግን ዲሞክራሲ ለሁሉም የሚፈልገዉን የሚሰጥ ስርአት አይደለም። ለብዙሃኑ የመምራትን ስልጣን ለአናስው ደግሞ የመብትን ጸጋ ያጎናጽፋል እንጅ። አይ "አንድ ሽህ ሰዎች ተሳስተው አንድ ሰው ብቻ ልክ ሊሆን ይችላል፤ አምሳ አህዮች ቢያናፉ የአንድ መሰንቆ ያህል ጣእም ያለው ዜማ አያወጡም"  ማለት አይቻልም።  እኔ እኮ ተምሬያለሁ፣ ተመራምሪያለሁ፣ የማየው አይታያችሁም፣ የምሰማው አይሰማችሁም ፣ ዝም ብላችሁ ተከተሉኝ ማለት አይፈቀድም።

ታዲይ አንዳንዴ ሳስበው ይህ ይምንናፍቀው ዲሞክራሲ ሊቸረን የማይችለውን ቱሩፋት የምንጠብቅበት ይመስለኛል። ዲሞክራሲ አንድ እንድንሆን አያደርግነም፤ በልዩነታችን ምክንያት በጦር እንዳንፋለም እንጅ። ዲሞክራሲ በፍቅር እንድንኖር አያደርገንም፤ ጠባችንን በሃሳብ እና በድጋፍ ማሰባሰብ እንድንፈታ እንጅ። ለዚህም ነው መቻቻል፣ መከባበር፣ እና አንዱ ሌላውን መርዳት አስፈላጊ እሴቶች የሚሆኑት። ይህንን ከተረዳን እና ካደረግን ተስፋ አልን፤ አለበለዚያ ግን በዲሞክራሲ ስናሸንፍ የተሸነፍን እየመሰለን መቸገራችን እይቀርም። አለበለዚያ ግን ጀግኖቻንን እያሰርን እድሜ ልክ እየፈረድን፣ስህተቱን እኛው ሰርተን ተበዳዩን ይቅርታ እያስጠየቅን፣ አዲሱን ፍልሚያ ባሮጌው መንገድ እየተፋለምን መኖራችን ነው።

በዲሞክራሲ ስርአት ያንተን ህልም ሌሎች ላይ መጫን አትችልም፤ ያንተን አላማ ብታምንበትም ማሳመን ካልቻልክ ዳር ቆመህ መጮህ እንጅ መሃል ገብተህ መንጠቅ አትችልም። ታዲይ ዳር ያሉት ሲጮሁ መሃል ያሉት ወይም ነን የሚሉት አገር ተረበሸ፣ ሽብርተኞች ነገሱ ማለት አይችሉም። የምንናፍቀው በፍቅር የምንኖርበት ሃይማኖታዊ ስርአት አይደለም፤ዲሞክራሲ እንደዚያ ሊሆን አይችልምና። ልዩነታችንን እና ጭሆታችንን እንደ ሙዚቃ ማጣጣም አለብን። ያን ማድረግ ካልቻልን ይህ ስርአት ወይ ይጠበናል ወይ ይሰፋናል ማለት ነው። ወይ አድገን እስክንሞላው፣ ወይ አንሰን እስኪበቃን በማስተዋልና በጥንቃቄ በመረዳትም እንታገል።

Wednesday, 25 July 2012

በግጥም ስንተክዝ



የኑሮ ጎዳናን ማን መርጦ ይሄዳል

ሲሆን ይወደዳል ባይሆን ይለመዳል

Feb. 11 2012

**********************


ስለ እኔ፣ ስለ እኔ፣ ስለ እኔ አትበሉ
ስለ እናንተ አይደለም መጭው ዘመን ሁሉ፤
መሻገሩ አይቀርም ቢረዝምም ቢበዛም
ይከራያል እንጅ አገር አይገዛም።
       Feb. 12, 2012

*********************

ጥቁር እና ነጭ

ቀለም ነው ያገኘሁ? ቀለሙን ነዉ ያጣው?

እኔ ነኝ የጠቆርኩ? እሱ ነው የገረጣዉ?

ጠይቄ ሳልጨርስ...

ጅምር ጥያቄየን ጥያቄ ረጠው
....
እኛ ከነ ነጮ፣ እኛ ከነ ቡሬ፣ ከነ ወይና አንሰን
ለምን ማሰብ ፈለግን ቀለም ተንተርሰን?

Feb 14, 2012

************************
ህልሙን አስጠብቦ በልኩ እያሰፋ

ካላወቅኩት የለም

ካላየሁት የለም ብሎ እየደነፋ

ተስፋን በመሰለው እየተረጎመ

እዉነትን ባወቀው እየደመደመ
የማይገባኝ ንቋ አይገባም እያለ
እሱ ነው ጠላቴ ተስፋዬን የጣለ
ስለሰፋው ብቻ ህልሜን ያጣጣለ።

Feb 15, 2012

***********************

ሃሳብ ወዳጄ ነው መንገድ ያሳየኛል

በዚህ በዚያ ሂደህ እዚህ ትደርሳለህ ብሎ ይመክረኛል

ዳሩ ይህ ወዳጄ መጥፎ ጠባይ አለው

ደከመኝ አይልም ሳነሳው ስጥለው

ሳባዝት ሳደቀው ስቆርጥ ስቀጥለው።

Feb 16 , 2012

*****************************

ሲቀለኝ በደስታ ሲከብደኝ በሃዘን

አልለካም አለኝ ህይወት አልመዝን

Feb 23, 2012

***************************

አምናዬን ጎትቼ አቆምኩት ከፊቴ

አየሁት በትኩረት ሞገትኩት አብዝቼ

ሂሳቡ ሲሰራ እኔ ሆንኩ ባለ ዕዳ

ግን ደግሞ ተፅናናሁ ...

ካልገባዉ ይሻላል ከርሞ የተረዳ

March 15, 2012

***************************

ከህይወት ባህር ላይ ያሳብ መረብ ጥየ ተስፋን አጠምዳለሁ

የማየውም ባያምር ከማይበት መንገድ ብርታት አገኛለሁ

March 25, 2012

****************************

የታመቁ እንባዎች ጉንጭ የናፈቃቸው
የሽሽት፣ የጭንቀት፣ የክፋት ስር ናቸው።
May 29, 2012


***************************

እንግዲህ ተስፋየን በደመና ጭኜ ላዝንበው ለራሴ

የህይወት በጋዬን የኑሮ ሃሩሬን ቢያርቀው ከነፍሴ
አምናና ዘንድሮን ዘንድሮና ከርሞን አንድ ላይ አስሬ ፊቴ ቁጭ ላርጋቸው
ትዝታም ምኞትም ሃሴትም ጭንቀትም ያሳብ ልጆች ናቸው።

June 17, 2012

Tuesday, 24 July 2012

በምታውቀው ልክ መኖር


                                 
በምታውቀው ልክ እንደመኖር ከባድ ነገር የለም። እስቲ አስቡት ከልጅነታችሁ ጀምሮ የተነገራችሁን ፣ የተረዳችሁትን እና የተቀበላችሁትን ። 
-ጊዜህን ባግባቡ ተጠቀም የተባላችሁበት ዘመን ዘመን የለውም።
-የምትናገረውን እጥፍ ያህል አዳምጥ ተባላችሁም ይሆናል( ይህን መርህ ተናጋሪውም አድማጩም ቢተገብሩት ምን እንደሚፈጠር ባይታወቅም።)
-ለነገ አትጨነቅ
-በራስህ ተማመን
-ሃሳቡን አንጅ ሰውየውን አትቃወም
-ሃጥያቱን እንጅ ሃጥያተኛዉን አትጥላ
-አታጭስ  አትቃም  አብዝተህ አት  ታምኝ ሁንጠንክረህ ስራ
በርትታህ ተማር
ኧረ ስንቱ   የሰው ልጅ የህይወት ትግል እንዲህ በማወቅ፣ በመቀበል እና በመርዳት ነገርግን በእውቀት ልክ መተግበር ባለመቻል የተሞላ ነው።

ሊያርመው፣ ሊያሻሽለው፣ ሊቀይረው የሚፈልገው ምንም ነገር የሌለው ሰው አይቸ አላውቅም። ካወቃቻሁ አደራ አንድትነግሩኝ። ምናልባት እሱ እያንዳንዱን ድርጊቱን በስሜት ፣ እንደተመቸው ወይም በወቅቱ እንደመሰለው ሳይሆን በሚያምንበት መርሁ የመራ መሆን አለበት።

ማድረግ ያለብንን እናውቃለን፤ ማድረግ ያለብንን ሁሉ ግን አናደርግም። የተሻለውን እና የተቀደሰውን መንገድ እንገነዘባለን፤ ያንኑ መንገድ መከተል ግን በቀላሉ አይሆንልም። በዚህም የተነሳ ህይወታችን ተወጥነው ባልተቋጩ እቅዶች፣ ተጀምረው ባልተፈጸሙ መንገዶች የተሞላ ነው። አንድ ቀን፣ ቃ አንድ ቀን ማድረግ የምንፈልገው ነገር በጣም ብዙ ነው።   አንድ ቀን ግን እንደሚመጣ የህይወት ተሞክሮም ሆነ የተፈጥሮ እውነታ ማርጋገጫ አልሰጠንም፤ አይሰጠንምም። በርግጥ ቀናት ይመጣሉ፤ እኛ እንደምንጠብቃቸው እርግጠኛ ባንሆንም። 

ትልቁ ትግል በምታውቀውና በተቀበልከው መንገድ ዛሬን መኖር ነው። ትልቁ ድል በምታውቀው ልክ ዛሬን መኖር ነው። መልካም ትግል።

Tuesday, 3 July 2012

በዝምታ መዋሸት?


 ከጓደኞችህ ጋር እያዎራህ/ሽ ነው እንበል። ስለሌላ አንተ ስለምታውቀው ሰው እያወራችሁ ነው። ስለምታወሩት ጉዳይ ጠንቅቀህ ታውቃለህ ነገር ግን መናገር ስላልፈለክ ዝም አልክ። በዝምታህ እያዋሸህ ነው?

 በቅርብ የተዋውቅከው ሰው ወይም እንበል ጓደኛህ በልጅነቱ ስላሳለፈው እና ስላለፈበት ድህነት ያጫውሃል። ስለሚያዎራው ነገር ጠንቅቀህ ታዉቃለህ፣ አንተም ያለፍክበት ስለሆነ። ነገርግን የሚነግርህን በጥሞና አዳምጠህ ስለ ራስህ ሳትነግረው ወሬ ቀየርክ። በዝምታህ እየዋሸህ ነው?

 የምትኖሪው ካገር ውጭ ነው እንበል። ኑሮን ለማሸነፍ የምሰሪውን ስራ ባታፍሪበትም አትኮሪበትም። ስለዚህ አገር ቤት ካሉ ዘመድ ጓደኞችሽ ጋር ስታዎሪ የስራሽን አይነት ሆነ ብለሽ አትጠቅሽም። በዝምታሽ እየዋሸሽ ነው?

 በወንጀል ተጠርጥረህ ፍርድ ቤት ብትቀርብ ወንጀሉን መፈጸም አለመፈጸምህን ስትጠየቅ ዝም ካልክ፣ዝምታህ አልፈጸምኩም እንደማለት ይቆጠርልሃል። ይህ ግምት የሚወሰደው፣ እስኪረጋገጥብህ ድረስ ነፃ ሁነህ የመገመት መብት ስላለህ ነው። በነገራችን ላይ እጅ ከፈንጅ ብትያዝ እንኩዋን ይህን መብትህን አትነጠቅም። ከነጠቁህ ወይም ሲነጠቅ ካየህ በህግ አምላክ ብለህ መጮህ ትችላለህ። የሆነው ሆኖ፣ ወንጀሉን የእውነት ፈጽመህ ቢሆን በህሊና ፍርድ ቤት ሲመዘን በዝምታህ እየዋሸህ ነው?

 በመጨረሻ ይህችን ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ “Lying is done with words and also with silence” የሚል አባባል ማንበቤ መሆኑን ሳልገልጽላችሁ ጽሁፌን ብጨርስ ኖሮ በዝምታ መዋሸት ይሆንብኝ ነበር?