Sunday 18 May 2014

የቴድሮስ አድሃኖምን የፌስ ቡክ ፔጅ አንላይክ ከማድረጌ በፊት የጻፍኩት መግቢያ



ዞን ናይኖች ይፈቱ እያልን ስንጮህ ጭሆታችንን እንደ ሙዚቃ እያጣጣሙት መሆኑን ለማስረዳት ያህል እንዲያውም የጠረጠርናቸው በሽብርተኝነት ነው ብለውን አረፉ። እንግዲህ ኢሜላቸው ሲበረበር ህገመንግስታዊ ያልሆነ ሃሳብ ተገኞቶበት ይሆናል። መቼስ ምን ይደረግ? እነሱ በድርጊት የማይጥሱት፣ ግለሰቦች ወይም ተቃዋሚዎቻቸው በሃሳብ የሚጥሱት ህገ መንግስት ነው ያለው።  ከዞን ናይኖች መታሰር ወዲህ ስለ አንድ ነገር ልጽፍ እነሳና አቋርጬ እተወዋለሁ። "ምን ዋጋ አለው?" እልና እተወዋለሁ። አንዳንድ አገራችንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የፌስ ቡክ ውይይት ሳይ ሁሉ እጅ እጅ ይለኛል። እነሱም የፈለጉት ይህንን ነው። ያሰሩት ዞን ናይኖችን ይሁን እንጅ ለማሸማቀቅ የፈለጉት ሁላችንንም ነው። መልእክቱ ለእያንዳንዱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ በድፍረት ቀና ብሎ መናገር የሚጀምርንና የሚያስብን ሰው ሁሉ የሚመለከት ነው። ብርቱካን ሚዴቅሳ ላይ የሆነውም ይሄ ነው። አገር ውስጥ ሆኖ መንግስትን መቃወም፣ በራስ ስም እና ምስል በግልጽ ተቃውሞ መናገር መንግስትን ማመንንም ይጠይቃል። እንጅ እንደ ኤርትራ ባለ አገር ለምሳሌ ዞን ናይኖችን የመሰለ ሰው ማግኘት አይቻልም። ይሄ መንግስት ዞን ናይኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የፍርሃቱን መጠን ብቻ ሳይሆን ያሳየው፣ ዞን ናይኖች በቀጥታም ባይሆን በስር አቱ ላይ ያሳደሩትን እምነት ነው የሰበረው። በግልጽ  የ አይነ መረብ ዘመቻ ሲያካሂዱ የነበሩ ሰዎችን በህብዕ እንደተደራጁ አድርጎ ማቅረብ፣ ተልካሻ መከራከሪያዎችን እያቀረቡ ትልቅ ነገር እንደተነገረ እያስመሰሉ መመጻደቅ፣ ያንንም በህግ የበላይነት ስም እንደሚደረግ እያስመሰሉ ራስን ማድነቅ ከመደጋገሙ የተነሳ እንኳን በታሰሩት ላይ ባልታሰርነው በ አንዳንዶቻችን ላይም የስነ ልቦና ቶርቸር እየተፈጸመብን እንዳለ እንድቆጥረው ያደርገኛል።

 ስለዚህ ጉዳይ ስንወያይ አንድ ጓደኛዬ በቀልድ መልክ "ቀጣይማ የምትታሰረው አንተ ነህ" ይለኛል። እኔ ደግሞ መልሼ በቀልድ መልክ "አንተን ካሰሩህ መሳሪያ ይዤ ወደ ጫካ ነው የምሄደው" እለዋለሁ። ከዛ ሁለታችንም እንሳሳቃለን። ቀጠል አደርግና "እኔም ብታሰር  ፌስ ቡክ ላይ ካሉ ሰዎች ውስጥ እነ እንትናና እነ እንትና "መንግስት ያደረገው ልክ ነው" ወይም ደግሞ "ፍትሃዊው የህግ ስርአታችን የሚለውን እስክንሰማ ድረስ እስራቱን አንቃወምም ይሉ ይሆናል እኮ" እለዋለሁ። እውነት ነው። ናትናኤል  በቅርቡ ምናልባትም ተመሳሳይ ውይይት ከቤተሰቦቹ እና ከቅርብ ጓደኞቹ ጋር እንዳደረገ መገመት እችላለሁ። እኔን ከናትናኤል የሚለየኝ ነገር ቢኖር እኔ የሱን ያህል ቆራጥነት የሌለኝ መሆኔ ይመስለኛል። እሱ ዲሞክራሲን ለኢትዮጵያ በሚመኘው ልክ እኔ አልመኝም ይሆናል። አሁን ከታሰሩት ውስጥ ከበፍቃዱ ውጭ የፌስ ቡክ ጓደኛዬ የሆነው እሱ ነው። በጣም አጨቃጫቂ በሆኑ ወቅቶች እንኳን ሰውን የሚያስቀይም ነገር ሲናገር አይቼው አላውቅም። አስታውሳለሁ መለስ መሞቱ እንደተረጋገጠ  "የኢትዮጵያ ህዝብ መለስን አልቅሶ ይቀብረዋል፤ ሃዘኑም የማስመሰል አይሆንም፤ ለዚህም በጣም እርግጠኛ ነኝ፤ ሌላ ነገር የሚጠብቅ ካለ የስነ ልቦና ዝግጅት ያድርግ" አልኩ። በዚህ አባባሌ ውስጥ የሚሆነውን ከመተንበይ አልፌ እንዲሆን የምፈልገውን እየተናገርኩ በመሆኑ በእርጋታ በአስተያየቴ እንደማይስማማ ሲገልጽልኝ አስታውሳለሁ። ከዚያ ውጭ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ የሰ ብ ዓዊ መብት አያያዝ በኃይለ ማርያም አስተዳደር ሊሻሻል ይችላል የሚለውን የቀን ቅዠቴን ፌስ ቡክ ላይ አክቲቭ በነበረበት ጊዜ ይጋራኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይሄ አስተዳደር በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ የሚታሰርበት ይሆናል ብሎ ግን ጨርሶ የገመተ አይመስለኝም። 


የነዚህ ልጆች መታሰር ቢያንስ  በአይነ መረብ በመሰረትነው የውይይትና የክርክር ማህበረሰብ ላይ የነበረንን የይስሙላ እኩልነት ነው ያፈረሰው። እንደዚህ ቀደሙ እንኳን ለምሳሌ እንደ እስክንድር መንግስትን የሚያበሳጩ ተከታታይ ጽሁፎች አልጻፉም። ከሰብአዊ መብት ተቋማት ጋር መስራት ነውር ነው ከተባለ ያንን እንዲያቋርጡ ጠርቶ ማናገር በቂ ነበር። በግሌ እንደምጠረጥረው አርቲክል አስራ ዘጠኝ የተባለው ድርጅት ገና በመስከረም ወር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብ አዊ መብት ጉባኤ በ አመቱ ኢትዮጵያ ላይ ለሚያካሂደው ግምገማ እንዲረዳ በሚል ያወጣው በጣም ዝርዝር ሪፖርት ውስጥ ምናልባት እነዚህ ልጆች ተሳትፈው ይሆናል።ለሰ ብ አዊ መብት መከበር መስራት ወንጀል ከሆነ፣ የሚፈለገው ሰብአዊ መብትን መጣስ ህጋዊ እንዲሆን ነው ማለት ነው። በጥር ወር ይሄው ድርጅት ሰርቶ ባወጣው በኢትዮጵያ ስላለው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሁኔታ በሚዳስስ ዶክመንታሪ ላይ አሁን ከታሰሩት የዞን ናይን አባላት መካከል ሁለቱ ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸዋል። አርቲክል አስራ ዘጠኝ የተባለው ድርጅት እነዚህን ልጆች ማግኘቱን ለመደበቅ ያደረገው አንዳችም ሙከራ እንዳልነበረ ያሳያል። ሌላው ቀርቶ የተለየ እቅድ እንደነበረ ለማስመሰል እየተደረገ የሚቀርበው ድርጅቱ ለጋዜጠኞች የሚሰጠው ሴኩሪቲ ነክ ስልጠና በዚሁ ዶክመንታሪ ላይ በድርጅቱ የአፍሪካ ሃላፊ በግልጽ ይጠቀሳል። እናም በጋሃድና በግልጽ የሆነውን ነገር ልክ በህቡ እንደተካሄደ ወንጀል እያደረጉ ሰዎችን ማዋከብ፣ ነጻነታቸውን መንፈግ፣ የግል ህይወታቸውን እና ከሰዎች ጋር የሚያደርጉትን የሃሳብ ልውውጥ እየበረበሩ ወንጀል የሚሆን ነገር በእግር በፈረስ መፈለግ የፍትህ ስራ ሳይሆን በራሱ ወንጀል ነው። አዎ መንግስት ይፈራል፤ የህዝብ አመጽ ይፈራል። በተለያየ ምክንያት ሰዎች ይህን አይነት አመጽ ሊናፍቁ፣ ሊፈልጉ፣ እንደሚፈልጉ ሊናገሩ ይችላሉ። መንግስት ስለሚፈራ ብቻ ግን ሳይተነኮስ፣ ይሄ ነው የሚባል ነገር ሳይፈጠር እየዘለለ ሰላማዊ ዜጎችን እያነቀ ወደ እስር ቤት የሚወስድ ከሆነ ፍርሃቱ ወደ በሽታ ተቀየረ ማለት ነው። ፍርሃት ሲበዛ ደግሞ ጥሩ አይደለም። ባገራችን "የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል" የሚባል አባባል አለ። 


 የኢትዮጵያ ህዝብ ስርአቱን በ አመጽ መቀየር ቢፈልግ ኖሮ መለስ ታመመ ተብሎ ምድረ ኢህአዴግ ሲሸበር አያለቀሰም እየጸለየም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር በመፍቀድ ፋንታ አጋጣሚዉን ተጠቅሞ የሚፈራውን ነገር ባደረገ ነበር። በነገራችን ላይ በወቅቱ እየቀጠለ የነበረው የሙስሊሞች ተቃውሞ እንኳን በሃዘኑ ምክንያት ተቋርጦ እንደነበር ማስታወስ ግድ ይላል።ለ አመጽ የሚያነሳሳ ጥሪ በወቅቱ መኖሩን የሚክድ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። ሌሎች ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድረስ ጥሪ ስለተደረገ ብቻ ሰው ለአመጽ አይነሳም።  በሃይለማርያም አስተዳደር በመለስ ጊዜ ከነበረው የሰ ብ አዊ መብት አያያዝ እና የዲሞክራሲ ሁኔታ የሚሻሻል ነገር ይኖራል ብለን ስንጠብቅ የሚሰጠን ምላሽ እነ ናትናኤልን በሽብርተንነት መክሰስ ከሆነ ለያውም በተልካሻ ምክንያት እኔ እንደ ጠብ ያለሽ በዳቦ ነው የምቆጥረው። ይህን የምለው የኢትዮጵያ ህዝብ ዞን ናይኖች ታሰሩ ብሎ ጎዳና ላይ ወጥቶ ፍቱልን ይላል ብዬ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠው የዲሞክራሲ ተስፋ እውነት እየመሰለው ትንሽ ቀና ቀና ከማለት ውጭ የደርግን እና የኢሳያስን ያህል ጭቆና መሸከም የሚችል ህዝብ ነው። 


የጊዜው መንግስት እየሄደበት ያለው አቅጣጫ ሳይተነኮሱ አንድ ሰው ዝም ብሎ ቁጭ ባለበት ሄዶ እንደመደብደብ አይነት ነገር ነው። ዞን ናይኖችን ማሰር ለኔ ያ አይነት እርምጃ ነው። ባጭሩ በግፍ እየተገፋን ነው። ለወትሮው የጊዜው መንግስት ልክ ነው ብዬ በማንምንበት ነጥብ ላይ ተቃዋሚ ነኝ ከሚል ከማንም ጋር ዞሬ የመከራከር ድፍረት ነበረኝ። ይሄ ድፍረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቶ ዞን ናይኖቹ ከመታሰራቸው በፊትም ተቃዋሚ ነኝ የሚለውን ወገን ሁሉ ባደባባይ መተቸትን እስከማቆም ድረስ  ደርሻለሁ። እና አንዳንድ ሰዎች ግልጽ አላማና ግብ በሌለው ጭፍን የተቃውሞ ባቡር ውስጥ የተሳፈርኩ እስኪመስላቸው ድረስ በሚያስችል ደረጃ ከነበረኝ አቋም እየተገፋሁ ነው። ባንድ ወቅት አንድ ወዳጄ ለግንቦት ሃያ አከባበር በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ጥሪ ተልኮለት "ምን እኮ ይሄ ጥሪ ወረቀት ላንተ ነበር መላክ የነበረበት" ብሎ እስኪቀልድብኝ የጊዜውን መንግስት መልካም ጥረቶች በግልጽ ከመናገር ወደ ኋላ የማልል ሰው ነበርኩ። ከዚያ ተነስቼ ነው አሁን ያለሁበት ደረጃ የደረስኩት። በዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ገዢው ፓርቲ ቢያናድድህ በሆነ መንገድ ትቀጣዋለህ። እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር መንግስት አክት የሚያደርገው ሰዎች ከሌላ ፕላኔት መጥተው ድምጽ የሚሰጡት አስመስሎ ነው። የቅቡልነቱ(legitimacy) ምንጭ የምርጫ ኮሮጆ እንዳልሆነ ስለሚያውቀው ሊሆን ይችላል። ወይም ለአቅመ መናገር የበቁ ዜጎች እንደ መራጭ ዜጋ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ስለሚያያቸው ይሆን ይሆናል። ምንም ቢሆን ግን ዞን ናይኖች ላይ እየተሰራው ያለ ግፍ በግሌ በዝምታ አላልፈውም። የምችለው መጻፍ ነው። መጻፌና መናገሬን አላቋርጥም። ይህን የማደርገው ዞን ናይኖች ጓደኞቼ ስለሆኑ አይደለም። በመሰረቱ አሁን ከታሰሩት ውስጥ በአይነ ስጋ አይቼው እንኳን የማውቀው ዘላለምን ብቻ ነው፤ እሱንም በርቀት። ወይም ደግሞ ይህን የማደርገው ህጋዊና ህጋዊ ያልሆነው ነገር በተደበላለቀበት የኢትዮጵያ የተጨማለቀ የፖለቲካ ከባቢ አላማና ግቡ በማይታወቅ የተቃውሞ ፖለቲካ የምሳፈርበት ባቡር ስለሚኖር፣ ወይም የመታሰራቸው ፖለቲካዊ አንድምታ፣ መታሰራቸው በታሳሪዎቹ የግል እና የፖለቲካ ህይወት ያለው ውጤት ወይም ነገሩን ከተቃውሞ ስትራቴጂ እና ከሌሎችም ነጥቦች አንጻር በማየት አይደለም። በቃ በዞን ናይኖች ውስጥ እኔ አለሁ።  የጊዜው መንግስት ላለፉት ሃያ ምናምን ቀናት እያሰማን የነበረውን ጭሆት እንደ ሙዚቃ በመቁጠሩ ይግረማችሁ ብሎ ክሱን ወደ ሽብርተኝነት ለማሳደግ በመወሰኑ ብስጭቴን ለመግለጽ ያህል ላይክ አድርጌ ስከታተለው የነበረውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን የዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ፌስ ቡክ ፔጅ አንላይክ በማድረግ እጀምራለሁ። እርምጃዬ ሊያስቅ ይችላል። ይህን በማድረግ የማስተላልፈው መልዕክት የሚከተለው ነው፤ መንግስትዎ ናትናኤልን አንገቱን ካስድፋ በኋላ፣ የርስዎን ፈገግታ የማይበት አቅም የለኝም። ዞን ናይኖች ሲፈቱ መልሼ እከታተልዎታለሁ። 
ቸር ያሰማን። 

No comments:

Post a Comment