ቀደም ባለው ጽሁፍ ስለ ጭቃኔ ስለተሞላበት ማሰቃየት የተወሰኑ ሃሳቦችን ወርውሪያለሁ።
በወንጀል ተጠርጥረዋል ተብለው በእስር ቤት ከሚገኙት የዞን ናይን አባላት መካከል ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ የውስጥ እግራቸውን በመደብደብ
የማሰቃየት ተግባር እንደፈጸመባቸው ተናግረዋል የሚለውን አሰቃቂ ዜና ከሰማሁ በኋላ ነበር አስተያየቱን የሰጠሁት። የልጆቹን ያንን
ማለት ተከትሎ ፖሊስ ድርጊቱን አልፈጸምንም በሚል ስሜት ማስረጃ የላቸውም አለ መባሉንና ቶርቸር ህገ መንግስታዊ አለመሆኑን መግለጹንም
ሰምተናል። የኢትዮጵያ ፖሊስ እንዲህ አያደርግም አይባል ነገር በታሪካችን እና በተሞክሮአችን አስቀያሚ ነገሮችን ያለፍን ህዝቦች
ነን። እንደዚህ አይነት ነገር በራሳችንና በምንወዳቸው ሰዎች ላይ ሲፈጸም እንደማንፈልገው ሁሉ በሌሎችም ሰዎች ላይ እንዳይፈጸም
ከልባችን የምንፈልግ ከሆነ እንደዚህ አይነት አቤቱታዎችን ቶርቸር ህገ መንግስታዊ አይደለም ከሚል የ አፍ ቸርነት ባለፈ እርምጃዎች
መውሰድ አለብን።
እርምጃ መውሰድ ሲባል ምን ማለት ነው የሚለው ላይ ነው በዚህ ጽሁፍ የተወሰነ ነገር
ለማለት የምሞክረው። በመጀመሪያ ቶርቸር እጅግ ሰልጥነናል እያሉ በሚመጻደቁ ህዝቦች እየተፈጸመ አንዳንዴ ሲጋለጥ እጅግ አሳፋሪ ቅሌት
እየሆነ ያስቸገረ በተለይም ከመስከረም አስራ አንድ ጥቃት በኋላ እና ከኢራቅ አቡግራይብ እስር ቤት የ አሜሪካና የ አጋሮቿ ሃይል
የፈጸመውን የሰ ብ አዊ መብት ጥሰት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ካጋለጠ በኋላ በእጅጉ አነጋጋሪ የሆነ ጉዳይ ነው። አሁን እኛ የምናወራው
ሳሙኤል ጃክሰን በተወነበት Unthinkable በተሰኘ ልብወለድ ፊልም እንደታየው ሶስት ትላልቅ ከተሞችን የሚያወድም ቦንብ ቀብሮ
ቃል አልተነፍስም ስለሚል አይነት አሸባሪ አይደለም። እንደዛ ባለው ሁኔታ ስለምንወስደው አቋም በመከራከር ላይሆን የሚችለውን ወይም
ከስንት አንዴ የሚሆነውን ሁሌ እንደሚሆን በማስመሰል ትኩረታችንን ከሚሻው ጉዳይ ቀልባችንን ማራቅ አይገባም። ከዚያ ይልቅ ከጎናችን
እየተወሰዱ “በህግ ጥላ ስር” ከሆኑ በኋላ እንዲህ አይነት ነገር ተፈጸመብን ሲሉ ምን አይነት ምላሽ ሊኖር ይገባል? እንዲህ አይነት
ነገር እንዳይከሰትስ ምን አይነት ጥንቃቄ መወሰድ አለበት? ስለሚለው ነው መጨነቅ ያለብን።
መጀመሪያ የዞን ናይኖችን ጉዳይ እንደ መነሻ እናድርገው እንጅ ይሄ ጉዳይ ከሙስሊም
መፍት ሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መታሰር እና በሽብርተኝነት ከተፈረጁ አካላት ጋር ግንኙነት አላችሁ እየተባሉ የሚታሰሩ ሰዎችንም
ይመለከታል። ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሚከነክነኝ ነገር ነው። ምክንያቱ ደግሞ ኢቲቪ የሚያቀርባቸው ዶክመንታሪዎች ናቸው፤ በሽብርተኝነት
ወይም በሌላ በከባድ ወንጀል ዜጎች ተጠርጥረዋል በተባሉ ማግስት በኢቲቪ ስለጥፋታቸው ፕሮግራም ሲሰራ ባየሁ ቁጥር እነዚህ ሰዎች
ስቃይ ካልተፈጸመባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንኳን ሳይታይ ራሳቸውን እየወቀሱ እና ጥፋተኝነታቸውን እያመኑ በኢቲቪ ይቀርባሉ እያልኩ
እጠይቃለሁ። ይህን እንድል የሚያደርገኝ ሌላ ማንም አይደለም፤ ያ የፈረደበት ህገ መንግስት ነው። ስለ ህገ መንግስታዊ ስር አቱ
እና ስለ ህግ የበላይነት የሚጨነቁ ወይም እንጨነቃለን የሚሉ ህገ መንግስት የሚባለው ስለመብቶች የሚዘረዝረው ክፍሉንም የሚጨምር
መሆኑን የህግ የበላይነትም ተጠርጣሪን በማሰር ብቻ ሳይሆን መብቱንም በማክበር የሚገለጽ መሆኑን ደጋግመን ልናስታውሳቸው ይገባል።
ለመሆኑ ከላይ ከ ኢቲቪ ዶክመንታሪዎች ጋር አያይዤ ያነሳሁት ት ዝብት ምን ህገ መንግስታዊ መሰረት አለው? ተከተሉኝ።
የህገ መንግስቱ አንቀጽ አስራ ዘጠኝ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ስላላቸው መብት
ይዘረዝራል፤ ብዙ ሰው የሚያውቀውና ደጋግሞ የሚናገረው መብት የተያዙ ሰዎች በ አርባ ስምንት ሰ አታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ
መብት አላቸው የሚለው ነው። ዞን ናይኖችንና አብረዋቸው የታሰሩትንም በተመለከተ በእሁድ ፍርድ ቤት ተከፍቶ ይሄ መብታቸው ተከብሯል
ተብለናል።
ጥያቄው በዚሁ አንቀጽ የተዘረዘሩ ሌሎች መብቶችስ ተከብረውላቸዋል ወይ የሚለው ነው።
ለምሳሌ የዚሁ አንቀጽ ን ኡስ አንቀጽ አንድ ወንጀል ፈጽመዋል በመባል “የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ
በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት አላቸው” ይለናል። ይሄ እንደተደረገ የምናውቀው ነገር የለንም። ስለ ህግ የበላይነት የሚጨነቁት
የጊዜው መንግስት ሰዎች ይህን ሊያረጋግጡልን ይገባል።
ንኡስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ “የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት አላቸው፤ የሚሰጡት ቃል
ፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል መረዳት በሚችሉት ቋንቋ እንደተያዙ ወዲያውኑ ማስገንዘቢያ ሊሰጣቸው መብት አላቸው”
ይለናል። ይሄ በ አሜሪካ ፊልሞች ላይ ፖሊሶች ተጠርጣሪዎችን ሲይዙ ሲናገሩ በምናይበት መንገድ የኢትዮጵያም ፖሊስ ዝም ብሎ አፈፍ
አድርጎ እያዳፋ መውሰድ ሳይሆን ለተጠርጣሪው “በዚህ ወንጀል ተጠርጥረህ ነው የተያዝከው፣ ዝም የማለት መብት አለህ፤ ለፖሊስ የምትሰጠው
ቃል በፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብብህ ይችላል” በማለት እንዲገልጽለት ህገ መንግስታዊ ግዴታ አለበት ማለት ነው። ታዲያ ይህ
ህገ መንግስታዊ መብት ባለበት አገር እንዴት ነው ተከሳሾቹ ለኢቲቪ ዶክመንታሪ በሚጠቅም መንገድ ቃል ሲሰጡ የምናየው። መብታቸውን
ስለማያውቁ ነው እንዳንል በህገ መንግስቱ መሰረት እንዲነገራቸው ይጠበቃል። ፖሊሶቹ ህገ መንግስቱን ላያውቁት ይችላሉ እንዳንል፣
ከጸደቀ ሃያ አመት ሊሆነው ነው። እውነታውን በምርመራ ሂደት የሚያልፉት፣
መርማሪዎቹ እና የሚያዙአቸው ያውቁታል።
የህገ መንግስቱ አንቀጽ አስራ ዘጠኝ ንኡስ አንቀጽ አምስት ፖሊስ በማስገደድ ማስረጃ
እንዳይቀበል ለማድረግ በ አንድ በኩል “የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም
ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም” ይለናል። በሌላ በኩል ደግሞ “በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም” በማለት
ለማስፈረድ በሚል ሃሳብ የሚደረግን ማስገደድ ለማስቀረት ይጥራል። በዚህ ላይ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 424 እንደዚህ ያለውን ተግባር
የሚፈጽሙ ሰዎች ከወንጀል ክስ እንደማያመልጡ ይነግረናል። በዚህ ላይ ቶርቸር በ አመታት ብዛት በይርጋ የማይተለፍ ወንጀል መሆኑን
ስናስብ በህግ ደረጃ ያለው ጥበቃ ቀላል ነው የሚባል አለመሆኑን እንረዳለን።
ያም ሆኖ ግን ይህን ህግ ለመተግበር የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ ከሌለ፣ ተቋማዊ እና የ አሰራር
ስነ ስ ር አቱ ካልተዘረጋ፣ ተጨማሪ የመከላከያ ሙከራዎች ካልተደረጉ ተከሳሾች ፍርድ ቤት እየቀረቡ አቤት ባሉ ቁጥር ችላ ከተባሉ
ህግ ጉልበተኞች ደካሞችን የሚያደቁበት መሳሪያ እንደሆነ ይቀጥላል። ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ፣ ዞን ናይኖች ከታሰሩ በኋላ
በአርባ ስምንት ሰዓት ፍርድ ቤት እንደቀረቡ ቢነገረንም፣ የማንገላታት እና የማሰቃየት ተግባር እንዳይፈጸምባቸው ሊያደርጉ የሚችሉ
መብቶቻቸውን ግን ተነፍገው ነው የሰነበቱት። ቶርቸር እንዳይፈጸም መከላከል ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ የሆነውን ተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ
እንዲያገኙ የማድረግ መብት ከነፍግናቸው፣ ፖሊስ እነዚህ ልጆች ላይ ቤቱን ዘግቶ ምን እንደሚያደርግ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?
ያም ይቅር፣ ቢያንስ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደዚህ አይነት ቃል ሲናገሩ፣ ፍርድቤት ነገሩን የሚያጣራበት ወይም እንዲጣራ የሚያዝበት
የተደራጀ ስርዓት ከሌለ፣ ቢያንስ ተጠርጣሪዎቹን ሃኪም አይቷቸው ተደርጓል የተባለው ነገር መፈጸሙን እንዲያረጋግጥ ካልተደረገ፣ ቶርቸር
ህገ መንግስቱ ይከለክላል የሚል መፈክር ለመናገርማ የተለየ ስልጠናም ሆነ ስልጣን አይጠይቅም። ይህን ለማድረግ ግን ከፍተኛ የፖለቲካ
ቁርጠኝነት ይጠይቃል። አለበለዚያ ዳኛውም ቢሆን ለእኔስ ማን አለኝ ብሎ ሊፈራ ይችላል። የአሰራር ስርዓቱ አስቀድሞ ካልተዘጋጀ አንድ
የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ለእንደዚህ አይነት ነገር ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ስለማያውቅ ያለው አማራጭ “ቶርቸር እኮ
በህገ መንግስቱ ተከልክሏል” ማለት ብቻ ይሆናል።
ታሳሪዎቹ ለ አስር ቀን ሙሉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ው ለው ምርመራ እየተደረገባቸው ጠበቃ
እንዳያገኛቸው ስለተደረገበት ምክንያት ጠበቃቸው ሲገልጽ፣ ፖሊስ ሌላ ስራ ይበዛብኛል እያለ ነው ብሎናል። የህግ ባለሙያ እኮ እንዲያገኛቸው
የሚያስፈልገው ፖሊስ እንዳያሰቃያቸው፣ እነሱን ከ አለም ሁሉ ነጥሎ እያስፈራራም እያታለለም ራሳቸውን የሚወነጅሉበት ቃል እንዲሰጡ
እንዳያደርግ ነው። ነገ ጠበቃ እንኳን ሳያገኛቸው የሰጡትን ቃል ኢቲቪ ላይ ፕሮፓጋንዳ ሲሰራበት ስናይ የህግ የበላይነት አድናቂዎች
ምንም የመብት ጥሰት እንዳልተፈጠረ በፕሮግራሙ ላይ እንድንወያይ ይጠይቁን ይሆናል። እድሜ ይስጠን ብቻ።
ቸር ይግጠመን!!
No comments:
Post a Comment