Tuesday 27 November 2012

መረዳት መርዳት ነው።


  • መረዳት መርዳት ነው።


ይህ አረፍተ ነገር ሁለት ትርጉም ነው ያለው። አንዱ የሌሎችን እርዳታ መቀበል በራሱ መርዳት ነው የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ ሌሎችን ሰዎች መረዳት(understand) ማድረግ እርዳታ እንደማድረግ ነው የሚል ትርጉም አለው። ብዙ ጊዜ ይህን አገላለጽ እጠቀመዋለሁ። የምጠቀመው ግን በሁለተኛው ትርጉሙ ነው። በእርግጥ በመጀመሪያ ትርጉሙም ስሜት እንዲሰጥ ሊደርግ ይችል ይሆናል። ማን ያውቃል? የተቸገረ የምታበላው፣ የተጠማ የምታጠጣው ለራስህ ጽድቅ እስከሆነ ድረስ ችግረኛው በመቸገሩ አንተ ራስህን የምትገልጽበት እና ጽድቅን የምታገኝበት መንገድ ስለፈጠረልህ እየረዳህ ነው የሚል ክርክር የሚያቀርብ ሰው አይጠፋም።

እኔ ግን መጠቀም የምፈልገው በሁለተኛው ትርጉሙ ነው። በእውነቱ ብዙ ጊዜ እንነጋገራለን እንጅ አንረዳዳም። አንዳችን አንዳችንን ባለመረዳታችንም የተነሳ፣ በመረዳዳት  understand በመደራረግ ልናገኘው እንችል የነበረውን እረፍት ራሳችንን እንነፍጋለን። በቸገረህ ጊዜ ችግርህን የማያቃልልህ ቢሆን እንኳ ችግርህን የሚረዳህ ሰው ማግኘት ምንኛ መልካም ነገር ነው። በጨነቀሽ ጊዜ ጭንቀትሽን ችሎ የሚያቀል ሰው ባይገኝ እንኳ የሚረዳ ሰው ማግኘት ምንኛ መልካም ነው። አዎ መረዳት መርዳት ነው።

እንግዲህ መረዳት መርዳት ከሆነ አለመረዳት መጉዳት ነው ሊባልም ይችላል። ነገር ግን ነገሩ በ ሉታዊ እና በወቀሳ መንገድ ከሚቀርብ ይልቅ በ አወንታዊ መንገድ ቢቀርብ የተሻለ ነው። ከዚህ ጋር አያይዤ አንድ ዛሬ በ አእምሮዬ እየተመላለሰ ስላለ ሃሳብ ልግለጽ። በመረዳት እርዱኝ።

በሁለት ሰዎች መካከል ያለ ርቀት በሁለት ነጥቦች መካከል እንዳለ እርቀት አይደለም። በሁለት ሰዎች መካከል ያለው ርቀት ርቀቱን መለካት ከምትጀምርበት አቅጣጫ ይወሰናል- ነው የሚለው ሃሳቡ። ፌስ ቡክ ላይ ለጥፌዋለሁ(The distance between two persons is not like the distance between two points. In case of persons, the distance depends on which side you start to measure) በመረዳት  የረዱኝ ሰዎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ። ለማለት የፈለኩት እንዲህ ነው። በሁለት ነጥቦች መካከል ያለ ርቀት ሲባል፣ አካላዊ ርቀትን የሚወክል ነው። ወረቀት ላይ ሁለት ነጥቦች ምልክት አድርገህ ከየትኛውም ነጥብ ተነስተህ ብትለካ ርቀቱ ያው ነው። በሰዎች መካከል ያለ ርቀት ስል ግን የቅርበት፣ የጓደኝነት፣ የፍቅር፣ የመተሳሳሰብ ርቀት ማለቴ ነው። እሱ እንደ ወንድም የሚያይህን ሰው፣ አንተ እንደ ሩቅ ሰው የምታየው ከሆነ በመካከላች ሁ ያለው ርቀት ካንተ ተጀምሮ ሲለካ ረጅም ሲሆን፣ ከሱ ተጀምሮ ሲለካ ግን በጣም አጭር ነው። ያመንኩት ከዳኝ ብሎ ሰው የሚያማርረው፣ ለልቡ ቅርብ የሆነን ሰው፣ በመካከላቸው ያለው ርቀት ከሌላኛው ወገን ተጀምሮ ሲለካ የገዘፈ መሆኑን ሳይረዳ በመቆየት ነው። ክንፍህን ዘርግተህ/ሽ  በደበበ ሰይፉ አገላለጽ "አበባ አሳብበህ/ሽ አዱኛ ሰብስበህ/ሽ የጠበቅከው/ሽው ሰው   የማይከሰትበት ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። ባልተጠበቀ ሁኔታ በቅንነት የምታስበው ሰው ኩርፊያ የሚያውጅብህ ሳታውቀው በመካከላችሁ ያለው ርቀት ከሱ ተነስቶ ሲለካ በጣም ገዝፎ ሊሆን ይችላል።

 ይህ ነገር የበለጠ በመረዳዳት እና እራስን በማስረዳት ሊቀረፍ ይችል ይሆናል። በእርግጠኝነት ግን መናገር አልችልም። ታዲያ በኔ ግምት ግድ አለን ለምንላችው መስተጋብሮች ርቀቱን እኩል ማድረግ ባይችል እንኳን ተቀራራቢ ማድረግ መልካም ነው። ለዚህም መረዳዳት ሳይረዳ አይቀርም። ሌሎችን ሰዎች በመረዳት እንርዳቸው። ሃሳቡን ያቀረብኩት ለራሴም ነው። በመርዳት እንርዳ፣ ፋይዳ ያላቸው ርቀቶቻችንን እናቀራርብ።

No comments:

Post a Comment