Tuesday 25 September 2012

በግጥም ስንተክዝ


የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የጻፍኳቸውን ግጥሞች መለስ ብዬ በመርመር ላይ እገኛለሁ። ጥቂት ያንድ ሰሞን ግጥሞችን ሳልበርዝ እንደተጻፉ ላካፍላቻሁ ወደድኩ። 

      ከጊዜ ውቅያኖስ
ባጭር ጭልፋ ጨልፎ ያችኑ አፍስሶ፣
                             እሷን ተንተርሶ፣
ነጥብ ታክል ነገር ታፋፋኝ ታኩራራኝ
                        ታሳድገኝ ብሎ፣
ትልቅ በመሰለው ሰው በጊዜው አድሮ፣ ሰው በጊዜው ውሎ
                                         ሰው በጊዜው ኑሮ
ምነዋ ባልሆነ የንፋሱ ሲሳይ ግልብ እንደገለባ፣
በስሜቱ ፍላት ገደል የሚገባ።
ከጊዜ ውቅያኖስ በጭልፋ ተጨልፎ
                    በዚያች ተነክሮ
እየረዘመበት ቀንና ሌሊቱ  ማታና  መአልቱ
እየተቸገረ እራሱ ኢምንቱ ለኢምንት ኢምንቱ
                                 ላጉል እሱነቱ
ተላላው ወንድሜ እኔ እኔ ያበዛል
ይውም ከኔነቱ ይሁን ላለው ጥቅሙ
                  ለምናብ አለሙ።
                       11-10-92 E.C.

****************************

“ያበደ” አላበደም
“ያበደ” አላበደም
“ያላበድን” አብደናል፣
“ጤነኞች”  የሆንን እውነቱ ጠፍቶናል፣
ፍቅር እንደ መጥፎ ያቅለሸልሸናል፣
መቻቻል እንደ ሬት ያንገፈግፈናል።
እኛ በራሳችን ብዙ ግፍ ሰርተናል፣
እየተገላለጥን እራቁት ሆነናል፣
እየተገፋፋን ተንጋለን አልቀናል፣
“ያበደ”  አላበደምያላበድን” አብደናል።

አለም በቃኝ ብሎ ብልህ ይመንናል፣
እብደት በቃኝ ብሎእብድ” ልብስ ያወልቃል፣
                           መርሳትን ያጠልቃል፣
እሱ ትክክል ነውያበደ” መች አብዷል
እኛ ግን ቀውሰን ፍቅርን አውልቀናል፣
ጤነኛ ነን ባዮችያላበድን” አብደናል።
17-10-92

**************************

ለ'ንቅልፍ ለ'ንቅልፍማ
ብርሃን ወገጋን ጨረር ተርከፍክፎ፣
ሁሉ ጎልቶ ሲታይ ጸዳል ተነጣጥፎ፣
                   አይንን ካልገለጡ፣
በብርሃን ፋና ለስራ ካልወጡ፣
በእውቀት በልጽገው ምንድንም ካልሰጡ፣
የማይበሩ ሻሞች ሆነው ከቀለጡ፣
ለንቅልፍ ለንቅልፍማ ጨለማን ማን በልጦ፣
የጸጥታው ድባብ ከሱ መቼ ታጥቶ፣
ለንቅልፍ ለንቅልፍማ ለወሬ ለቅዠት፣
ጨለማ ይሻላል ቁርጡን የለየለት፣
ቢገልጡም ቢከድኑም ለውጥ የማይኖርበት።
17-10-92

**********************

የበሰለ ተስፋ
የሮጠው እግር የሮጠው፣
ሩጫውንም ባይጠግበው፣
ሩጫው ግን በቃው ጠገበው፣
             እድሜ ገደበው።
የፈሰሰው ተስፋ ተስፋው፣
ሩቅ መስሎ ከቅርብ ያለው፣
ግድቡን ደርሶ ተመልሶ፣
ት ዝታ ብቻ ቀረው።
በዚህ ዛሬ
ቆዳ ሳይናደድ ሲኮሳተር፣
ወገብ ሲሰግድ ወደምድር፣
አይነ ስጋ ሲደክም
የት ዝታ ምጣድ ሲግም፣
ስራውን አበጥሮ
ተግባሩን ጋግሮ
የተጋገረው ት ዝታ
በዚህ ማታ
ከ’ድሜ ገበታ
ት ዝታ ብቻ ሳይሆን ተስፋም ነው፣
                  የበሰለ ተስፋ፣
የሞት ድልድይን ላለመፍራት፣
                መንፈስን የሚያፋፋ።
                               20-10-92 E.C. 

No comments:

Post a Comment