Saturday, 11 August 2012

አስተሳሰብን ማናወጥ


ተመስገን ደሳለኝ ተከሰሰ የሚል ዜና በሰማሁ ጊዜ በጣም አዘንኩ። አስቀድመው በእስር ያሉ ጋዜጠኞች በተፈረደባቸው ከባድ ፍርድ አዝነን ሳንጨርስ ሌላ ክስ መጣ ስንባል ማዘን ሲያንሰን ነው። የምናዝነው በኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት እስካሁን ባለው የህግ አረዳድ እና አተረጓጎም እምነት ስለሌለን ብቻ አይደለም። ለዳኞቹም ቀጥተኛ ትዛዝ በቀጥታ ከመንግስት ይሰጣል ብለን ስለምናምን አይደለም። የምናዝነው፣ ዜጎችን መብት በተለይም የመጻፍ እና የመናገር መብት ለማጥበብ አገራችን መንግስት ቀን ከሌሊት ሲሰራ ማየት ቆሽታችንን ስለሚያሳርረው ነው። የአሁን ስርአት አድናቂዎች እና መዘውሮች ሊረዱልን ያልቻሉት አንድ ነገር ቢኖር፣ እነሱ እራሳቸውን በሚያሳምን ምክንያት ብዙሃኑ ህዝብ ስለሚወዳቸው ስልጣን ላይ ያሉ ቢሆን እንኳን፣ የማይቀበሉትን እና የሚያንገሸግሻቸውን ሃሳብ ሰምተው ችሎ የማደር ችሎታን ማዳበር የሚገባቸው ራሳቸው መሆናቸውን ነው። እኔ እስከምረዳው ድረስ፣ ጋዜጣ ለማንበብ የታደለው ኢትዮጵያ ህዝብ፣ ጋዜጣ የሚያነበው ህገ መንግስታዊ ስር አቱን ለማፍረስ አይደለም። ህገመንግስታዊ መብቱን ለመጠቀም እንጅ። ህገ መንግስታዊ ስርአቱ ደግሞ ባፋችሁ እንደነገራሁን በህዝቦች ሉአላዊነት ላይ የተመሰረተ ነው። ከመርሆቹ መካከል ሰብአዊ መብቶች የማይገፈፉ መሆናቸው ይገኝበታል። አሁን እንደ እኔ ሲቪክ ሲማር ላደገ ሰው በዚህ ስር አት ሙሉ ትምህርቱን ለተከታተለ ሰው፣ ቅድመ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ላየ ሰው፣ አሁን ያለንበት የህግ አተረጓጎም እና የመብት አረዳድ፣ ከመርዶ ጨርሶ አያንስም። አስተሳሰብንም ያናውጣል

ለማነኛውም ፋናን ዜና ካነበብኩ በኋላ የተጠቀሙትን ገለጻ በመጠቀም ተመስገን የተከሰሰባቸው የመሰሉኝን አንቀጾች መርጬ ለማውጣት ሞክሬያለሁ። አንብባችሁ ሌላው ቢቀር ክሱን የመሰርቱት አቃቢ ህጎች አንዳንዶቻችን እንደምናስበው ወንጀሉን አለመፍጠራቸውን መገንዘብ ትችላላችሁ። እርግጠኛ መሆን የምችልበት ነገር ግን ሃሳብን በነጻነት መግለጽ በተረጋገጠበት አገር እና ሀሳቡን የገለጸው ደግሞ ጋዜጠኛ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሲጀምር ክሱ መመስረቱ የተሳሳተ ነው ብዬ አማናለሁ። መንግስት ያለበትን ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት ረስቶ ጠላት የመሰለውን ማጥቂያ መሳሪያ አድርጎ መጠቀሙን አጠናክሮ መቀጠሉ ጭፍን የመንግስት አድናቂ ካልሆንክ በቀር ሊዋጥልህ አይገባም። እኛኮ የጸጋዬ ገብረመድህንን አገላለጽ ልዋስና እንሸሸግበት ጥግ አጣን። ተኮማተርን እኮ፣ ሃሳባችን ሁሉ ከሳ። ላገራችን በምንመኘው እና ባገራችን በምናየው መካከል ባለው ልዩነት የተነሳ አስተሳሰባችን ተናወጠ። 

ቀጥሎ አስቀድሜ እንደተናገርኩት የፋናን ዜና አንበቤ ተመስገን ደሳለኝ የተከሰሰባቸው የመሰሉኝን አንቀጾች ከወንጀል ህጋችን ፈልጌ አስቀምጫለሁ። ጋዜጠኛው ሲጽፍ አንቀጾቹን ጠቅሶ ቢሆን ኖሮ ከግምት እድን ነበር። የግምት አገር ነው ያለን- ምን ይደረግ።   http://www.fanabc.com/Story.aspx?ID=25306&K#.UCVMa6c8EbE.facebook

“አንቀጽ 257  መገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር
ማንም ሰው ከዚህ በላይ አንቀጽ 238  እስከ 242    አንቀጽ 246    እስከ   252 ድረስ ከተመለከቱት ወንጀሎች አንዱ እንዲፈጸም ለማደረግ ወይም ለመደገፍ
) በንግ ግር በስ እል ወይም በጽሁፍ አማካይነት በግልጽ የቀሰቀሰ እንደሆነ፣ ወይም
) ሽፍቶች(a band or a group) አገር ውስጥ ወይም አገር ውጭም ቢሆን እንዲቋቋሙ ያደመ፣ እቅድ ያወጣ ወይም የገፋፋ እንደሆነ፤ ወይም
) እንደዚህ በመሳሰሉት ሽፍቶች ቡድን የገባ፣ በእቅዱ የተባበረ፣ ወይም ትእዛዙን የተከተለ እንደሆነ፤ ወይም
) ከውጭ አገር መንግስት የፖለቲካ ወይም ሌላ ድርጅት፣ ወይም ከነዚሁ ወኪሎች ጋር ግንኙነት ያደረገ ወይም በምስጢር ግንኙነት የተባበረ እንደሆነ፤ ወይም
)የህዝቡን ሞራል ዝቅ ለማድረግና እምነቱን ወይም የመቋቋም ሃይሉን ለማፍረስ በማቀድ በተቀናጀ ዘዴ ትክክለኛ ያልሆነ፣ ጥላቻ የተሞላበት ወይም ያለውን አቋም የሚያፈርስ (insinuations calculated to demoralize the public and undermine its confidence) መረጃ በንግ ግር በጽሁፍ ወይም በስእል የበተነ ወይም ያስታወቀ እንደሆነ፤

በቀላል እስራት፤ ወይም ይህ አድራጎት ሊያስከትል ይችል የነበረው አደጋ በተለይ በጣም ከፍ ያለ እንደሆነ አስር አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል።’


“አንቀጽ 244...
ማንም ሰው በንግግር ወይም አድራጎት ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን አደባባይ አገሪቱን መንግስት ያዋረደ፣ የሰደበ፣ ስሙን ያጠፋ ወይም በሃሰት የወነጀለ እንደሆነ፣
ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም አምስት መቶ ብር በማያንስ መቀጮ ይቀጣል።
የስም ማጥፋት በሃሰት የመወንጀል፣ የማዋረድ ወይም የመስደብ ድርጊት ተፈጽሟል የሚባለው አንቀጽ 613  እና 615  መሰረት ነው።”

“አንቀጽ 486 የሀሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን ማነሳሳት
ማንም ሰው አገር ደህንነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ውጭ በሆነ አኳኋን ፣(Arts 240 , 257(e) & 261(a)
በመንግስት በህዝብ ባለስልጣኖች ወይም በስራቸው ላይ የሀሰት ወሬዎችን ጥርጣሬዎችን ወይም የሃሴት ሀሜታዎችን የሚፈጥር ወይም የሚነዛ ሰው፣ ከዚህም የተነሳ የህዝቡን አስተሳሰብ ያንወጠ፣ የቀሰቀስ፣ ወይም ለማናወጥ የሚችል እንደሆነ ወይም (Starts or spreads false rumours, suspicions or false charges against the government or public authorities or their activities , thereby disturbing or inflaming public opinion, or creating a danger of public disturbances; )
) በማናቸውም አይነት ማሳጣት ወይም ሌላ ዘዴ ጥርጣሬን ያስፋፋ፣ ጥላቻን ያነሳሳ ወይም የኃይል ድርጊት ወይም የፖለቲካ፣ የዘር ወይም የሃይማኖት ሁከት የቀሰቀሰ እንደሆነ፤

በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ፣ ወይም ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ከሶስት አመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል።”


በመጨረሻ እ.ኤ. አ  በ 1976    አመተ ምህረት የአውሮፓ የሰብአዊ መብት ፍርድቤት(Handyside v. the UK) ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ መብት የጻፈውን በጣም ታዋቂ አባባል በማስቀመጥ ላብቃ። በነገራችን ላይ የኛ ህገ መንግስታዊ ስርአት ሃሳብን በነጻነት ስለ መግለጽ ከዚህ የተለየ አረዳድ ሊኖረው የሚችልበት ህጋዊ ምክንያት የለም።

“Freedom of expression applies not only to ‘information’ or ‘ideas’ that are favorably received but also to those that offend, shock or disturb the State or any Sector of the population. Such are the demands of that pluralism, tolerance and broadmindedness without which there can be no “democratic society”. This means … that every “formality”, “condition”, “restriction” or “penalty” imposed in this sphere must be proportionate to the legitimate aim pursued.”

አንዳንዱ የአገራችን ሁኔታ፣ ምናለበት አስር ሃያ አመት ተኝቼ በተነሳሁ እና የሚመጣውን ባየሁት ያስብላል። ቸር ያሰማን።

No comments:

Post a Comment