ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግስት
ይህን መልእክት የምጽፍላች ሁ እስክንድር ነጋን ፈትታች ሁ ጉድ እንዳት ሰሩን ለማስጠንቀቅ ነው። የህግ የበላይነት ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምት ሰጡት ነገር እንደሆነ ባውቅም ሰው ሆኖ የማይረሳ የለምና አንዳንድ ማስታዋሻ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተሰማኝ።እስክንድር ነጋ ላይ ትኩረት ያደረኩት እስክንድር እስክንድር የሚሉ ሰዎች መብዛታቸውን እና ባልተለመደ መልኩ የእስክንድር እስራት ህገ ወጥ ነው የሚል አስተያየት በተባበሩት መንግስታት አላግባብ የሚፈጸሙ እስራቶችን የሚከታተል አካል(UN Working Group on Arbitrary Detention) የተሰጠ መሆኑ ለየት ያለ ነገር ሆኖ በማግኘቴ ነው። በመጀመሪያ ይሄ እስክንድር ነጋ የምትሉትን ወንጀለኛ አስራችሁ እስክታስተዋውቁኝ ድረስ ከስም በዘለለ ማወቄን እጠራጠራለሁ። አሁን እድሜ ለናንተ የህግ ማስከበር ተግባር እንጅ እንኳን እኔ የ አገሩ ዜጋ ቀርቶ፣ የኢትዮጵያን ስም በክፉ የሚያነሱ ሰዎች ሁሉ ያውቁታል። ደግሞ እንዴት ነበር ይጽፍ የነበረው ባካች ሁ፤ እሱን እያነበበ ነው ለካን ምድረ ፈረንጅ እስክንድር እስክንድር የሚለው፤ አይ እኛ እንዲህ አይነት ቀልድ አናውቅም። በህግ የበላይነት እና በህገ መንግስቱ የሚመጣብንን አንታገስም።
ታዲያ ዛሬ እኔ እንደ ደጋፊዎቻችሁ ጨከን ብዬ አንዳንድ ምክሮችን ልለግሳችሁ ወደድኩ። እስክንድርን ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እስክትሆን ድረስ እንዳትፈቱት፤ ይቅርታ መስጠት የሚባል ነገር እንዳታስቡት። በፍጹም። የኒዮ ሊብራል ሃይሎች አንድን አስራ ስምንት አመት ተፈርዶበት እስር ቤት የሚገኝ ወንጀለኛ ፍቱ የሚሉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ተራ ወንጀለኛ ነው፤ የፖለቲካ እስረኛ አይደለም፤ ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ በፍጹም እንዳትፈቱት። የተፈረደበት ሽብርተኛ በመሆኑ ንብረቱንም ውረሱ፤ በተባበሩት መንግስታት አላጋባብ የታሰሩ ሰዎችን ጉዳይ የሚከታተለው የባለሙያዎች አካል የእስክንድር እስራት ህገ ወጥ እና ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን አለም አቀፍ የሰብ አዊ መብት ሰነዶች የሚጻረር ነው ማለቱ በእውነቱ ስለ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ያለውን ዝቅተኛ እና እዚህ ግባ የማይባል እውቀት እና አስተሳሰብ የሚያሳይ በመሆኑ እንዳትሰሙት። የአሜሪካ መንግስትንም እንዳትሰሙት፤ እነሱም ቢሆን ስለ ህግ የበላይነት እና ስለ ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ ብዙም አያውቁም። አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች የሚባሉት በተለይ በሰብ አዊ መብት ስም የሚነግዱ በመሆናቸው ጆሮ አትስጧቸው።ደግሞ የገዛ ህዝባችሁን የፈለጋችሁን ብታደርጉ እነሱ ምን አገባቸው? ይህ የህግ የበላይነት ጉዳይ እና የኢትዮጵያን ህገ መንግስት የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ እስክንድርን በፍጹም እንዳትፈቱት። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ቆይቶ፣ በቀጣይ ምርጫ ተመርጦ ወይም በሌላ ሰው ተተክቶ፣ ሌላ አምስት አመት ቆይቶ ሌላ ምርጫ ተካሂዶ፣ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ተተክቶ ቆይታው እስኪገባደድ ድረስ እንዳትፈቱት።
ኢትዮጵያ ለጊዜው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል አባል በመሆኗ ከላይ የተጠቀሰው አካል የሰጠውን አስተያየት ተቀብላ የእርምት እርምጃ እንድትወስድ የሚጠብቁ ሰዎች ቢኖሩም ያንን የማድረግ ህጋዊ ግዴታ እንደሌለባት ግን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ግፋ ቢል ነገሩ በተለያየ አጋጣሚ በተነሳ ቁጥር አንገት መድፋት ነው፤ ግፋ ቢል ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን እንደሚያሳድድ አምባገነን መንግስት ሆኖ መታየት ነው፤ ሌላ ምን ይመጣል፤ ግፋ ቢል "አዲስ ንጉስ እንጅ ለውጥ መቼ መጣ" የሚለውን የቴዲ አፍሮን ዘፈን ለ አቶ ሃይለማሪያም የሚጋብዙት ሰዎች መብዛት ነው፤ ሌላ ምን ይመጣል፤ በዚያ ላይ እስክንድር አሁን የሚፈታ ከሆነ ይሄ የተደረገው መለስ ሞተው ሃይለማርያም በመተካቱ ነው እያሉ የ አቶ ሃይለማሪያምን ስም ከፍ ከፍ በማድረግ የመለስን ስእብና ሊያኮስ ሱ ሊሞክሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። ይሄው ትናንት ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ ብሎ ቢቢሲ ሃይለማሪያም ስለተተኩ ነው ለማለት ሞከረ አይደለም እንዴ?
ደግሞ Freedom Now የሚባል ድርጅት እስክንድርን አስፈታለሁ እያለ ይንቀሳቀሳል አሉ። የሚገርም እኮ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ተራ ወንጀለኛ የጠፋ ይመስል እስቲ አሁን እስክንድር ነጋን ምን አስመረጣቸው? ኧረ Committee to Free Eskinder Nega የሚባልም አለ አሉ። የሚገርም እኮ ነው ይሄ ሁሉ ሰው የሚንጫጫው ለ አንድ ተራ ወንጀለኛ መሆኑ አለም ምን ያህል ለህግ የበላይነት ያለው ቁርጠኝነት እየወረደ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ሌላው የሚገርመው ነገር መለስ ሞተ ሃይለማርያም ተተካ ብለው ሃያ ዘጠኝ የሰብ አዊ መብት ይመለከተናል የሚሉ ድርጅቶች ለ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎችንም የፖለቲካ እስረኞች የሚሏቸውን ተራ ወንጀለኞች ለመፍታት ጠይቀው ነበር አሉ። እንዴት ያለ ነገር ነው? ስለ ህግ የበላይነት አያውቁም እንዴ? ስለ ህግ የሚያውቁት ነገርም ያለ አይመስልም፤ እስክንድር ነጋ ማለት እኮ ህገ መንግስታዊ ስ ር አቱን በ ሰላማዊ ሰልፍ ለመናድ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ሰው ነው።
ይሄ ሁሉ ጫጫታ ምንም ግምት ሊሰጠው የማይገባ ከንቱ ነገር ነው። እስክንድር ነጋ የመሰለ ሽብርተኛ ቢፈታ ህዝባችን ሊያሳልፍ የሚችላቸውን እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፣ ሽብር እና ስጋት ከግምት ውስጥ አስገብተን ማሰብ አለብን። ከሁሉም በላይ ደግሞ የወንጀል ህግ አላማ እና የህግ የበላይነት ሽብርተኞችን፣ እና ለማህበረሰብ ደህንነት አደገኛ የሆኑ ሰዎችን ለቀን ህዝቡ ላይ አደጋ እንዲጋረጥ እንድናደርግ አይጋብዘንም። እናም አደራ! እስክንድርን እንዳትፈቱት።
No comments:
Post a Comment