Monday, 3 June 2013

አደራ እስክንድርን እንዳትፈቱት-ምጸታዊ ምክር

ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግስት 
ይህን መልእክት የምጽፍላች ሁ እስክንድር ነጋን ፈትታች ሁ ጉድ እንዳት ሰሩን ለማስጠንቀቅ ነው። የህግ የበላይነት ጉዳይ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምት ሰጡት ነገር እንደሆነ ባውቅም ሰው ሆኖ የማይረሳ የለምና አንዳንድ ማስታዋሻ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተሰማኝ።እስክንድር ነጋ ላይ ትኩረት ያደረኩት እስክንድር እስክንድር የሚሉ ሰዎች መብዛታቸውን እና ባልተለመደ መልኩ የእስክንድር እስራት ህገ ወጥ ነው የሚል አስተያየት በተባበሩት መንግስታት አላግባብ የሚፈጸሙ እስራቶችን የሚከታተል አካል(UN Working Group on Arbitrary Detention)  የተሰጠ መሆኑ ለየት ያለ ነገር ሆኖ በማግኘቴ ነው።  በመጀመሪያ ይሄ እስክንድር ነጋ የምትሉትን ወንጀለኛ አስራችሁ እስክታስተዋውቁኝ ድረስ ከስም በዘለለ ማወቄን እጠራጠራለሁ። አሁን እድሜ ለናንተ የህግ ማስከበር ተግባር እንጅ እንኳን እኔ የ አገሩ ዜጋ ቀርቶ፣ የኢትዮጵያን ስም በክፉ የሚያነሱ ሰዎች ሁሉ ያውቁታል። ደግሞ እንዴት ነበር ይጽፍ የነበረው ባካች ሁ፤ እሱን እያነበበ ነው ለካን ምድረ ፈረንጅ እስክንድር እስክንድር የሚለው፤ አይ እኛ እንዲህ አይነት ቀልድ አናውቅም። በህግ የበላይነት እና በህገ መንግስቱ የሚመጣብንን አንታገስም። 

ታዲያ ዛሬ እኔ እንደ ደጋፊዎቻችሁ ጨከን ብዬ አንዳንድ ምክሮችን ልለግሳችሁ ወደድኩ። እስክንድርን ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እስክትሆን ድረስ እንዳትፈቱት፤ ይቅርታ መስጠት የሚባል ነገር እንዳታስቡት። በፍጹም። የኒዮ ሊብራል ሃይሎች አንድን አስራ ስምንት አመት ተፈርዶበት እስር ቤት የሚገኝ ወንጀለኛ ፍቱ የሚሉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ተራ ወንጀለኛ ነው፤ የፖለቲካ እስረኛ አይደለም፤ ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ በፍጹም እንዳትፈቱት። የተፈረደበት ሽብርተኛ በመሆኑ ንብረቱንም ውረሱ፤ በተባበሩት መንግስታት አላጋባብ የታሰሩ ሰዎችን ጉዳይ የሚከታተለው የባለሙያዎች አካል የእስክንድር እስራት ህገ ወጥ እና ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውን አለም አቀፍ የሰብ አዊ መብት ሰነዶች የሚጻረር ነው ማለቱ በእውነቱ ስለ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ያለውን ዝቅተኛ እና እዚህ ግባ የማይባል እውቀት እና አስተሳሰብ የሚያሳይ በመሆኑ እንዳትሰሙት። የአሜሪካ መንግስትንም እንዳትሰሙት፤ እነሱም ቢሆን ስለ ህግ የበላይነት እና ስለ ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ ብዙም አያውቁም። አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች የሚባሉት በተለይ በሰብ አዊ መብት ስም የሚነግዱ በመሆናቸው ጆሮ አትስጧቸው።ደግሞ የገዛ ህዝባችሁን የፈለጋችሁን ብታደርጉ እነሱ ምን አገባቸው? ይህ የህግ የበላይነት ጉዳይ እና የኢትዮጵያን ህገ መንግስት የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ እስክንድርን በፍጹም እንዳትፈቱት። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ቆይቶ፣ በቀጣይ ምርጫ ተመርጦ ወይም በሌላ ሰው ተተክቶ፣ ሌላ አምስት አመት ቆይቶ ሌላ ምርጫ ተካሂዶ፣ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ተተክቶ ቆይታው እስኪገባደድ ድረስ እንዳትፈቱት። 

ኢትዮጵያ ለጊዜው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል አባል በመሆኗ ከላይ የተጠቀሰው አካል የሰጠውን አስተያየት ተቀብላ የእርምት እርምጃ እንድትወስድ የሚጠብቁ ሰዎች ቢኖሩም ያንን የማድረግ ህጋዊ ግዴታ እንደሌለባት ግን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ግፋ ቢል ነገሩ በተለያየ አጋጣሚ በተነሳ ቁጥር አንገት መድፋት ነው፤ ግፋ ቢል ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን እንደሚያሳድድ አምባገነን መንግስት ሆኖ መታየት ነው፤ ሌላ ምን ይመጣል፤ ግፋ ቢል "አዲስ ንጉስ እንጅ ለውጥ መቼ መጣ" የሚለውን የቴዲ አፍሮን ዘፈን ለ አቶ ሃይለማሪያም የሚጋብዙት ሰዎች መብዛት ነው፤ ሌላ ምን ይመጣል፤ በዚያ ላይ እስክንድር አሁን የሚፈታ ከሆነ  ይሄ የተደረገው መለስ ሞተው ሃይለማርያም በመተካቱ ነው እያሉ የ አቶ ሃይለማሪያምን ስም ከፍ ከፍ በማድረግ የመለስን ስእብና ሊያኮስ ሱ ሊሞክሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። ይሄው ትናንት ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ ብሎ ቢቢሲ ሃይለማሪያም ስለተተኩ ነው ለማለት ሞከረ አይደለም እንዴ?

ደግሞ Freedom Now የሚባል ድርጅት እስክንድርን አስፈታለሁ እያለ ይንቀሳቀሳል አሉ። የሚገርም እኮ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ተራ ወንጀለኛ የጠፋ ይመስል እስቲ አሁን እስክንድር ነጋን ምን አስመረጣቸው? ኧረ Committee to Free Eskinder Nega የሚባልም አለ አሉ። የሚገርም እኮ ነው ይሄ ሁሉ ሰው የሚንጫጫው ለ አንድ ተራ ወንጀለኛ መሆኑ አለም ምን ያህል ለህግ የበላይነት ያለው ቁርጠኝነት እየወረደ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ሌላው የሚገርመው ነገር መለስ ሞተ ሃይለማርያም ተተካ ብለው ሃያ ዘጠኝ የሰብ አዊ መብት ይመለከተናል የሚሉ ድርጅቶች ለ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎችንም የፖለቲካ እስረኞች የሚሏቸውን ተራ ወንጀለኞች ለመፍታት ጠይቀው ነበር አሉ። እንዴት ያለ ነገር ነው? ስለ ህግ የበላይነት አያውቁም እንዴ? ስለ ህግ የሚያውቁት ነገርም ያለ አይመስልም፤ እስክንድር ነጋ ማለት እኮ ህገ መንግስታዊ ስ ር አቱን በ ሰላማዊ ሰልፍ ለመናድ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ሰው ነው።

ይሄ ሁሉ ጫጫታ ምንም ግምት ሊሰጠው የማይገባ ከንቱ ነገር ነው። እስክንድር ነጋ የመሰለ ሽብርተኛ ቢፈታ ህዝባችን ሊያሳልፍ የሚችላቸውን እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፣ ሽብር እና ስጋት ከግምት ውስጥ አስገብተን ማሰብ አለብን። ከሁሉም በላይ ደግሞ የወንጀል ህግ አላማ እና የህግ የበላይነት ሽብርተኞችን፣ እና ለማህበረሰብ ደህንነት አደገኛ የሆኑ ሰዎችን ለቀን ህዝቡ ላይ አደጋ እንዲጋረጥ እንድናደርግ አይጋብዘንም። እናም አደራ!  እስክንድርን እንዳትፈቱት።

Tuesday, 14 May 2013

ይድረስ ለፖለቲካ ቁማርተኞች



አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል አስራ ሁለት ሰዎችን ገደለ የሚለውን አሳዛኝ ዜና ከሰማን ወዲህ ይህችም መጥፎ አጋጣሚ እንደሌላው ክስተት ሁሉ የፖለቲካ ትርፍ ማካበቻ ሆና ታይታ ብዙ አስገራሚ ምላሾችን ታዝበናል። የፖለቲካ ቁማር ትልቁ ችግር አንዱን ወይንም ሌላውን ቆማሪ ደግፈህ ብትናገርም፣ ሁለቱን ብትቃወምም፣ ዝም ብትልም የጨዋታው አካል ነህ። ህይወትህ ባይነካ ስሜትህ ይነካል። ዛሬህ ባይነካ ነገ ህ ይነካል።  ስለዚህ ዝም ማለት አልቻልኩም። የምናገረው የመቀባጠር ያህል ቢሆንም፣ ለፖለቲካ ቁማርተኞች እና (ከነሱ ጋር የምጋራው ማንነት ካለኝ ለኔም ይሆናል) ይህን ማለት ወደድኩ።

የፖለቲካ ቁማርተኞች ሆይ የሚያስጨንቃችሁን እናውቃለን፤ እንቅልፍ የሚነሳችሁን እናውቃለን። እንኳን በንጹሃን ተራ ሰዎች ሞት ይቅርና ታላቁ መሪያችሁን በሌላ ወገን አምባገነኑ የምትሉትን  ገዥያችሁን  አስከሬን አጋድማችሁ ትቆምራላችሁ። የእኛ እንባ የሞኝነት እንባ ናት። የኛ ሃዘን የጅልነት ሃዘን ናት፤ ለናንተ። እንኳን የተደረገ ያልተደረገም ነገር ቢሆን ፈጥራችሁ ታወራላች ሁ፤ የፖለቲካ ትርፍ ካገኛች ሁ፤ ጓደኝነት አታውቁም። ቅንነታችሁን ሽጣችኋል፤ ጸጉር ትሰነጥቃላችሁ፤ በእያንዳንዷ ኮሽታ የፖለቲካ ትርፍ ይታያችኋል፤ ያስጎመዣችኋልም። እውነቴን እነግራችኋለሁ፣ የያዛችሁትን ስልጣን ላለመልቀቅ (ከመንግስት ወገን ያላችሁት)  የሌላችሁን ስልጣን ለማግኘት (ተቃዋሚ ነን የምትሉት) የዛሬዋን ኢትዮጵያ በዛሬዋ ሶርያ ለመለወጥ ዝግጁ ናችሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። 

ቁጥር ነን ለናንተ እኛ፤ ስንራብ በቁጥራችን ትከራከራላችሁ፤ ስንገደል በቁጥራችን ትከራከራላችሁ፤ ስንፈናቀል በቁጥራችን ትከራከራላችሁ፤ በቃ ቁጥር ነን ለናንተ እኛ። 
ሃይማኖቶቻችን ተረቶች ናቸው ለናንተ፤ እንደ ጭቃ ጠፍጥፋችሁ እንደገና ብትሰሩን ሁሉ ያምራችኋል፤ ታሪካችን ተረት ናት ለናነተ፤ እንደሚመቻችሁ መልሳችሁ ብትጽፏት ደስ ይላች ኋል፤ ለእውነት ደንታ የላችሁም እናንተ፤ በስልጣን እና በጉልበት እውነትን ተፈጥራላችሁ። መጀመሪያ የሌለ አላማ ትፈጥራላችሁ፤ ለዚያ አላማ እንድንሞትለት ታደርጋላችሁ፤ ከዚያ ይሄ እኮ ሰው የሞተለት አላማ ነው ትሉናላች ሁ።  ቆይ እኛ የናንተ ህልም ስእል ማሳመራይ ቀለሞች ነን? በምንድነው የገዛችሁን?  በእውቀት ነው የገዛችሁን? በገንዘብ ነው የገዛች ሁን? በፍቅር ነው የገዛችሁን? ምንድነው የልብ ልብ የሚሰጣችሁ? 

እኛ ጥሎብን ብዙ የህይወት እይታችን የተቀዳው ከሃይማኖትና ከባህል። ቅንነት፣ ፍቅር፣ የዋህነት፣ ጓደኝነት፣ መተሳሰብ ወዘተ ያማልሉናል። ሰላም እንፈልጋለን። ሃብት ብናገኝ ከድ ህነት ብንወጣም እንወዳለን። ዘፋኝ እንኳን የምንወደው "ፍቅር ያሸንፋል" የሚል ከሆነ ነው።  ለናነተ ይሄ ሁሉ የቁማር ገንዘብ ነው። እኛ ግብ የምንለው ለናንተ መሳሪያ ነው። ስልጣንን እና ባለስልጣንን ለመነቅነቅ በምንወዳቸው እና በምናከብራቸው እሴቶቻችን ላይ ትረማመዳላች ሁ። ስልጣንን ለመጠበቅ በእንባችን፣ በሃዘናችን፣ በ ሃይማኖታችን፣ በታሪካችን፣ በቋንቋችን፣ በብሶታችን፣ በተስፋችን፣ ባለን ነገር ሁሉ ትቆምራላችሁ። 

ኑሮአችሁን ለማሻሻል እንፈልጋለን ትላላችሁ፤ ይወዱናል ብለን ስንዘናጋ እንደማትወዱን ታሳዩናላችሁ። የምትፈልጉት እኛን አደራጅታችሁ መንዳት ነው። እናንተ እንድታስቡ እኛ እንድንከተል። ተረታችሁን እየሰማን እንድናንቀላፋ። 

ልዩነታችን፣ ራሳችንና ሌሎችን የምናይበት መንገድም ዋነኛ የቁማር ገንዘባችሁ ነው። የፖለቲካ ትርፍ ካያች ሁ፣ ፍር ሃት፣ ጥርጣሬ ሌላው ቀርቶ ጥላቻ እንኳን ስር ቢሰድ ደንታ የላችሁም። እንደየሁኔታችሁ ስልጣንን ለመጠበቅ ወይም ስልጣንን ለመነቅነቅ የማትጫኑት ቁልፍ የለም። ለሃይማኖታችን ያለን ቀናኢነት፣ ለቋንቋችን እና ለራሳችን ያለን ክብር፣ ስለሌሎች ህዝቦች ያለን የተሳሳተ አመለካከት፣ የተጠቃሚነት መንፈስ፣ የተጎጅነት መንፈስ፣ ሁሉም ከመጫን የማትመለሷቸው ቁልፎች ናቸው። ለዚሁ ቁማርና ትርፍ ስትሉ ጀግና ትገድላላችሁ፣ ጀግና ትፈጥራላችሁ፣ እውነት ትሰውራላችሁ፣ እውነት ትፈበርካላች ሁ፣ ጠላት ትፈጥራላችሁ፣ ወዳጅ ትመስላላችሁ፣ ትገድላላችሁ፣ ታሳድዳላችሁ፣ ታዋርዳላችሁ፣ ትዋረዳላችሁ። 

የፖለቲካ ቁማርተኞች ሆይ፣ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሆይ፣  ለቁማራችሁ እና ለንግዳችሁ የስነ ምግባር ገደብ አበጁለት። 

Wednesday, 10 April 2013

ማንነት ያልተበደርነው እዳ



ሰዎች የሚያሳዝናቸውን ነገሮች ይመርጣሉ?  ሰዎች የሚያስደነግጣቸውን ነገር ይመርጣሉ? ሰዎች የሚያስከፋቸውን ነገር ይመርጣሉ?  አላውቅም! እኔ ግን ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቀሉ ስለተባሉት ሰዎች ከሰማሁ ወዲህ፣ አዝኛለሁ፣ ለጉዳዩም ብዙ ትኩረት ሰጥቻለሁ። በእርግጥ ምንድነው የሆነው?  ምን ያህል ሰዎች ናቸው የተፈናቀሉት? በምን አይነት ሁኔታ ነው የተፈናቀሉት?  በመኪና አደጋ ሞቱ የሚባሉት ሰዎች ነገር እውነት ነው?  ድርጊቱ የተደረገብት ዝርዝር ምክንያት፣ እና የተደረገበት አግባብ ምንድነው? ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጥያቄዎች ነበሩን፤ የምናገኘው በጣም ጥቂት መልሶችን ነበር።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛ አለ? እያልኩ ሁሉ ራሴን መጠየቅ ጀምሬ ነበር። አዲስ አድማሶች፣ መጀመሪያውንም ቢሆን ይህን ጉዳይ ለህዝብ ትኩረት ያበቁት እነሱ ናቸው፣ አሁን ደግሞ ስፍራው ድረስ በመሄድ እንዲህ አንጀት የሚበላ ግን ስለጉዳዩ እንድናስብ የሚያስችል ጽሁፍ አቀረቡልን። እጅግ ምስጋና ይገባቸዋል። ለጽሁፉ አዘጋጅ ደግሞ የተለየ ምስጋና።

ጽሁፍን ያነበብኩት በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ ሆኜ ነበር። ራሴን በተፈናቃዮቹ ቦታ አድርጎ ለማሰብ አይጠበቅብኝም ነበር። ምክንያቱም እኔ ራሴ ተፈናቃዮቹን ነኝ።  እነዚህ ሰዎች ናቸው የተባሉትን ሁሉ ነኝ። ይህን የምለውም በከፍተኛ ሃዘን ነው። ጎጃሜ ናቸው ብለው ካሳደዷቸው፣ ጎጃሜ ነኝ። አማራ ናቸው ብለው ካሳደዷቸው፣ አማራ ነኝ፤ ደገኛ ብለው ካሳደዷቸው፣ ደገኛ ነኝ። ኢትዮጵያዊ ብለው ካሳደዷቸው፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ። በዚህም የተነሳ ይሆናል ህመሙ ዘልቆ የተሰማኝ።

አንድ የፌስ ቡክ ጓደኛዬ ስለነዚህ ሰዎች መፈናቀል ወሬ ሲደጋገምበት ጊዜ ይመስላል፣ "ቆይ እነዚህ ሰዎች አማራ ክልል የሰፈሩ ሽናሻዎች ቢሆኑና ቢፈናቀሉ ኖሮ ነገሩ እንደዚህ ይጋነን ነበር?" ብሎ ጠይቋል። ጥያቄው መልካም ነው። ትግራይ ኦን ላይን የተባለው ዌብ ሳይት ደግሞ በፊውዳል ኢትዮጵያ በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ በአማራ ገዥ መደቦች የተፈጸሙ ግፎችን የሚዘረዝር ጽሁፍ የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች ጉዳይ ዋና ርእስ በሆነበት ሰሞን አውጥቷል። ለነገሩ ጸሃፊው የግንቦት ሃያ ድል በአል እየተቃረበ ስለሆነ ነው ጽህፉን ያወጣሁት ያለው። አንዳንዶቻችን በልባችን ተወው ባክህ እንኳን ይችን የዝምብ ጠንጋራ እናውቃለን ብለን አልፈነዋል። ለጻፈበት ምክንያት ሳይሆን በጽሁፉ ውስጥ ላካተታቸው የታርክ እውነቶች እና የማህበረሰብ ትውስታዎች ስንል ግን ተገቢውን ክብር አልነፈግነውም።

በእውነት ግን ማንነት ያልተበደርነው እዳ ነው፤ ወደን በላያችን ያላወጣነው ሸክም። እውነተኛዋን ኢትዮጵያን ልተዋወቅ ወደ ጅማ ዩንቨርሲቲ ከማቅናቴ በፊት ነበር ለዚህ ምስክርነቴን የሰጠሁት።

ተወለድኩ
አባት አልመረጥኩም፣
እናት አልመረጥኩም፣
አገር አልመረጥኩም፣
ወገን አልመረጥኩም፣
ሆኜ ያገኘሁትን መርጬው አልሆንኩም። (7/2/96 E.C.)

ከላይ ያልኩትን ሁሉ የጻፍኩት የቤንሻንጉል ክልል ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ ወስኗል መባሉን ከመስማቴ በፊት ነው። ዛሬ ደግሞ ስለችግሩ ዘግበዋል ሲባሉ ያልሰማናቸው ጋዜጦች ስለመፍትሄው ውሳኔ ነግረውናል። እንደ አዲስ አድማስ ባይሆንም እነሱንም ቢሆን በመጠኑ እናመሰግናቸዋለን።  አንዳንድ ነገሮችን ማለት ወደድኩ።

አንድን የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል በሚጋራው የፖለቲካ፣ የዘር፣ የዜግነት፣ የብሄር፣ የባህል፣ የሃይማኖት ወይም የጾታ ማንነት መነሻ ማሳደድ(persecution) የሰብአዊነት ዝቅጠት ብቻ አይደለም። በ አለም ላይ አስከፊ ከሚባሉ ወንጀሎች አንዱ የሆነው በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸመ ወንጀል የመሆን ሁሉ እድል አለው።(see article 7 of the Rome Statute of the International Criminal Court) ይህ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ እንደኢትዮጵያ ባሉ የብዝሃነት ችግር በሌለባቸው አገሮች። ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛቱ ወደር የሌለው ብሄር ነው። በ አማራ ክልል ውስጥ ግን አናሳ ብሄር ነው። አማራ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው ብዙ ብሄር ነው፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ግን አናሳ ብሄር ነው። ማንነት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ቁማር ያችን አገር መውጫ የሌለው ጥፋት ውስጥ ነው የሚከታት። የቡድን እና የግለሰብን መብት በጋራ ለማክበር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ትክክለኛውን ሚዛን ማግኘት ከባድ ቢሆንም፣ ከእንደዚህ አይነት እብደቶች መታቀብ ካልተቻለ እጅግ እጅግ አሳሳቢ ነው።

ከ አምስት አመት በፊት የኬንያን ምርጫ ተከትሎ የሆነውን የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና የክልል ባለስልጣናት ቀረብ ብለው ሊያጤኑት እና ሊመረምሩት ይገባል። ዛሬ የኬንያ ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቃው ሰው ምን አድርገሃል ተብሎ በምን ወንጀል እንደተከሰሰም ቀረብ ብለው ሊያጤኑት ይገባል። የኪራይ ሰብሳቢነት፣ እና የ አፈጻጸም ስ ህተት ቋንቋ ለእንደዚህ አይነት አስቀያሚ ተግባር በጣም ይጠበዋል፤ አይበቃውም።

በሌሎች አገራት በግጭት ጊዜ በደም ፍላት የሚደረግ ተግባር በኢትዮጵያ በ አማን አገር እየተደረገ ነው ሲባል የማይደነግጥ ሰው መኖር የለበትም። አንድ ሰው የገደለ፣ አንድ ሰው የሰረቀ፣ አንድ ሰው የሰደበ፣ አንድ ሰው የደበደበ ምን ያህል ይቀጣል?   የአንድ ሽህ ሶስት መቶ አርባ ስድስት ቤተሰብ ህይወት ያመሳቀለ ሰው ምን ያህል ይቀጣል?  ይህ የ አፈጻጸም ስ ህተት ተብሎ መታለፍ የለበትም።

ባለስልጣናቱ ይሏቸዋል የሚባሉ አንዳንድ ንግግሮች እውነት ከሆኑ፣ የቤንሻንጉል ክልል አንዳንድ ባለስልጣናት የክልሉ የብሄር ቁጥር ሚዛን እንዳይበረዝ በከፍተኛው እንደሚሰጉ ያመለክታል። ከሌላ ክልል የሚመጡ ማህበረሰቦች ቁጥር እየበዛ ከሄደ፣ በ ገንዘብ ያላቸው ጥንካሬ እየጨመረ ከሄደ፣ ወደ ስልጣኑም መምጣታቸው አይቀርም የሚል ስጋት እንዳለባቸው ያስታውቃል። ይሄን ስጋታቸውን ተገቢ ስጋት አድርገውም የቆጠሩት ይመስላል። በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ እጅግ በጣም አደገኛ የዘር ማጽዳት(ethnic cleansing) ጽንስ አለ። እነሱ ግን ይህንን ህግ እንደማስፈጸም አድርገው ነው ያሰቡት።

የሆነው ሆኖ ይህን በጣም አስቀያሚ ተግባር ከመፈጸም ለመከላከል ባይቻልም፣ ለማረም ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ማውቅ መልካም ሆኖ ታይቶኛል። የተፈጸሙ ነገሮችን ለማጣራት እና ለሌሎችም ሰዎች መማሪያ ይሆን ዘንድ እውነቱን ለህዝብ ለማሳወቅ ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጣ የ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ ሪፖርት ቢያደርግ ደግሞ እጅግ በጣም የተሻለ ይሆን ነበር።

አንድ ሎተሪ አዙሮ ኑሮውን ይገፋ የነበረ ሰው፣ አንድ ጉልበቱን ሽጦ የሚያርስ አርሶ አደር፣ ባለመረጠው የማንነት ሸክም እዳ ከፋይ ሲሆን ማየት ግን ከሁሉም በላይ ያማል።
አዎ፤ ማንነት ያልተበደርነው እዳ፣ ያልመረጥነው ሸክም ነው። አንድም ሰው ቢሆን በማንነቱ ምክንያት ጥቃት ደረሰበት ሲባል ሁሉም ሰው በሚችለው አቅሙ ሁሉ ያንን ነገር ስ ህተት መሆኑን ከመናገር እና ከማውገዝ መቆጠብ የለበትም። ዛሬ ሁላችንም በስማችን የምንጠራ፣ በትምህርት ደረጃችን፣ በግለሰብ ደረጃ በምናንጸባርቃቸው ደግነቶች፣ መልካም ንግ ግሮች፣ መጥፎ ተግባራት ወዘተ የምንታወቅ ልንሆን እንችላለን። አንድ ቀን አንዱ ተነስቶ አለኝ የምትለውንም ሆነ/አለኝ የማትለውን ማንነት አሸክሞ ሊያጠቃህ ቢጀምር ያኔ ከሰውነት ወርደህ የሆነ ቡድን አባል መሆን ብቻ ወንጀልህ ይሆናል። በሁለተኛው አለም ጦርነት ጊዜ አይሁዶች ላይ የሆነው ይሄው ነው፤ በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የሆነው ይሄው ነው። በቦስንያ ሙስሊሞች ላይ የሆነው ይሄው ነው። የዛሬ አምስት አመት ገደማ ኬንያውያን አንዳቸው በሌላቸው ላይ ያደረጉትም ይሄው ነው። ለኢትይጵያ ህዝብ ከእነዚህ  በ አንዳቸውም ላይ የተፈጸመው አንድ መቶኛ እንኳን ሲፈጸም ያኔ ቀፎው እንደተነካ ንብ ተነስተን ያንን ማረም አለብን።

ዝምታው፣ ቸልታው እንዳለ ሆኖ የተፈጸመው ነገር ያሳሰባቸው ሰዎች ደጋግመው ሲናገሩ፣ "ይህን የሚለው አማራ ስለሆነ ነው?" "ይህን የሚለው ጎጃሜ ስለሆነ ነው?" "ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲል አልነበረም እንዴ?" ወዘተ አይነት እንደቀልድም ቢሆን የሚነገር ሃሳብ መስማት በጣም ያማል። ይህን ነገር ተከትሎ በሚከሰት ጭሆትና የአቤቱታው አቀራረብ፣ "የአማራ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ይለምልም" የሚለው የብአዴን መፈክር እየተሳካ ይሄዳል ብለው እንደሚደሰቱ ወይም እንደሚሰጉ ሁኔታቸው የሚያሳብቅባቸው ሰዎች እንዳሉ ማወቅ ያቃጥላል።

የሆነው ሆኖ፣ በእርግጥ እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ መጡበት የሚመለሱ ከሆነ፣ ከደረሰባቸው ሰቆቃ አገግመው፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እንደገና በሰላም የሚኖሩበት መንገድ በሚገባ መመቻቸት ይኖርበታል።