ከጥቂት ወራት በፊት አንድ ስዊድናዊ ተማሪ ስትፈራ ስትቸር ስለ አገራችን የፍትህ ስርአት እና የዳኞች ብቃት አንዳንድ ጥያቄዎች አነሳችልኝ። ይህ የሆነው ያገራችን አንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለት ስዊድናዊ ጋዜጠኞች ላይ የአስራ አንድ የአስራ አንድ አመት ቅጣት እንደወሰነ ሰሞን ነው። ለመገንዘብ ያዳገታት ነገር ቢኖር ተገቢ የህግ ትምህርት የተከታተለ ሰው እንዴት በህገ ወጥ መንገድም ቢሆን ለመዋጋት ሳይሆን ለመዘገብ ወደ ሌላ አገር የገቡ ሰዎችን በሽብርተኝነት እንደሚቀጣ ነው። ነገሩን ለማስረዳት የማደርገው ጥረት የባሰ የአገራችንን እውነታ እያወሳሰበባት ሲሄድ ይህ ነገር በነሱ ላይ የተጀመረ አለመሆኑን እና ሽብርተኛ ተብሎ ከተሰየመ ድርጅት ጋር በህገ ወጥ መንገድ ለዘጋቢዎች በተከለከለ አካባቢ በመገኘታቸው፣ መሃል አዲስ አበባ ተቀምጠው በሚጽፉት ጽሁፍ ተመሳሳይ ክስ ከሚመሰረትባቸው ያገሬ ሰዎች አንጻር የነሱ መከሰስም ሆነ ፍርዱ እንደማይገርመኝ ገልጬ፣ ይቅርታ ከጠየቁ ግን ሊፈቱ እንደሚችሉ በትህትና አስረዳሁ።
አሁን በይቅርታ ሲፈቱ ስለ እውነታው መለስ ብሎ ለማሰብ እድል አገኘሁ፤ በነዚህ ሁለት ሲውድናውያን ክስ ጉዳይ ብዙዎች ሲያዝኑና ሲተክዙ ተመልክቻለሁ፤ ተገቢ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ግን ወንጀል መፈጸማቸው ለማንም የተሰወረ አይደለም፤ በእርግጥ ወንጀሉ "ሽብርተኝነት"፣ ወይም "ሽብርተኘነትን መደገፍ" የሚለው ስም ሊበዛበት ይችላል። ወንጀል መሆኑን ለማወቅ የሄዱበት አውሮፓ የ አፍርካን ስደተኞች ምን እንደሚያደርግ መመልከት ይበቃል። የሚገርመው ነገር እነዚህ ሰዎች እንደ ስደተኛ አፍሪካውያን እንኳን እራሳቸውን ከችግር ለማዳን አይደለም ወደ እዚያ ያመሩት። ለመሄድ ሲወስኑ ራሳቸውን ችግር ውስጥ እየከተቱ መሆኑንም ቢሆን ጠንቅቀው ያውቁታል። በተያዙበት ቦታ እና ሁነታ ከዚህ የባሰ አደጋ ያላጋጠማቸው መሆኑ በእርግጥ እድለኞች ነበሩ የሚያስብል ነው፤ ይቅርታ ይደረግልኝና እኔ ከነሱ ይልቅ በጣም የሚከነክነኝ፣ በስደት ተቀምጠው ጻፉ ተብለው የተፈረደባቸው ወገኖቼ ናቸው፤ ይቅርታ ይደረግልኝና እኔን የሚከነክነኝ ምንም ይሁን በጻፉት እና በተናገሩት መነሻ ለእስር እና ለቅጣት የተዳረጉ፣ ምናልባትም ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እስክትሆን ድረስ በእስር ሊቆዩ የሚችሉ ያገሬ ሰዎች መኖራቸውን መረዳት ነው፤ ህግ ከለጠጡት የማይደርስበት ቦታ አለመኖሩን ስለሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ እና አመለካከት ያላቸውን ሰዎች የማሸማቀቅ እድሉ የሰፋ በመሆኑ ያሳዝነኛል፤ ብዙ ሰዎች ስለ ሌሎች ሰዎች የመናገር እና የመጻፍ መብት መጨነቅ ያለብህ እነዚሁ ሰዎች በሚጽፉት እና በሚናገሩት ስትስማማ ብቻ ይመስላቸዋል። ይህ የተሳሳተ አመለካከት ይመስለኛል፤ በሃሳቡ አለመስማማት አንድ ነገር ነው፤ በማትስማማበት ሃሳብ እና በወንጀል መካከል ግን ሰፊ ልዩነት አለ። አሁን በቅርብ አንድ የኢሳት ጋዜጠኛ አንድ የሻብያ የፕሮፓጋንዳ ባለሙያ ጋብዞ ስለ ኤርትራ ዲሞክራሲ እና ነጻ ፕሬስ ስብከት ሲያሰጠን፣ መለስን ከኢሳያስ ጋር ለማቀራረብ ጥረት ሲያደርግ በጣም አበሳጭቶኛል፤ ታዲያ ይህ ሰው ከጠላት ጋር በመተባበር ባገር ክህደት ተከሶ ቢፈረድበት ሃሳቡን አምርሬ ስለጠላሁት ፍርዱን እቀበላለሁ ማለት ነው? እንደዚህ መሆን የለበትም።
የማትፈልገውን እና የማይጥምህን ሃሳብ ዝም የማሰኘት ጽኑ ፍላጎት የአምባገነንት ዋና ምልክት ነው፤ ይህ አዝማሚያ በሁሉም ሰው ላይ አለ። በመንግስት ላይ በኖረ ጊዜ አደጋው ከፍ ይላል። "የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ" ልጆች ይህን ጽኑ ፍላጎታቸውን የሚወጡት ጠላቶቻችን የሚሏቸውን በመግደል ለዘላለም ዝም በማሰኘት ነበር። አሁን መሻሻል ቢኖርም አቅመ ቢስ ድምጾችን ሳይቀር የማፈን ጽኑ ፍላጎት መኖሩ ለማንም የተሰወረ አይደለም።
እስክንድር ነጋ እና ሌሎች በእስር ያሉ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ መፈለግ ያለብን ጻፉት ወይም አሉት ከሚባለው ነገር ጋር ከተስማማን ብቻ መሆን የለበትም፤ በተናገረው ወይም በጻፈው መስማማት አለመስማማት አንድ ነገር ነው፤ የ አስራ ስምንት አመት እስራት ሲፈረድበት ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ እና ምንም ነገር እንዳልሆነ ብሎም ጉዳዩ የህግ የበላይነት ጉዳይ ብቻ እንደሆነ አድርጎ መከራከር ያስተዛዝባል። በእርግጥ መንግስት እና ሌሎች ያገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች የህግ ሁኔታውን እንዳወሳሰቡት ለማንም የተሰወረ አይደለም፤ ጥቂት የማይባሉ በሁሉም መንገድ እንታገላለን የሚሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ በኩል፣ መንግስት ደግሞ በሌላ ወገን ሆነው ሰላማዊ እና ህገመንግስታዊ ሊባል የሚችለውን እንቅስቃሴ ማጣበባቸው እሙን ነው። በሁሉም መንገድ እንታገላለን የሚሉቱ መፍትሄውን ከ ህግ ውጭ በመፈለግ፣ መንግስት ደግሞ ከህግ ውጭ በው ይይት፣ በድርድር፣ ገፍተው ሲመጡ ደግሞ በፍልሚያ ሊያገኝ የሚገባውን መፍት ሄ ከህግ ለማግኘት በመሞከር ህገ መንግስታዊ ስር አቱን በግልጽና በስውር ይፈታተኑታል። የሁለቱም አሰላለፍ ባጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት የተቀያየረ በመሆኑ የተመልካቹን የህዝብን አስተሳሰብ በከፍተኛው ያናውጣል።
ይህ ሰላማዊ እና ህገመንግስታዊ መንገድ በተጣበበ ቁጥር ሰዎችን በራሳቸው አእምሮ ውስጥ የቅድመ ምርመራ መሳሪያ አስገጥመው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ፤ ማሰብ ባያቆሙም፣ ያሰቡትን መናገር ያቆማሉ፤ መታዘብ ባያቆሙም፣ ይታዘቡትን መናገር ያቆማሉ። ታዲያ በዚህ የተነሳ ጋዜጠኞች በጻፉ ቁጥር በመብታቸው እየተጠቀሙ ይሁን ወንጀል እየፈጸሙ ለማወቅ አይችሉም። በዚህ የተነሳ በሚፈጠረው ድባብ የሚሰማህን በጻፍክ ጊዜ ሰዎች "ፖለቲከኛ መሆን ፈለክ እንዴ?" "መታሰር ፈለክ እንዴ?" 'ሽብርተኛ መሆን ፈለክ እንዴ?" እያሉ በቀልድም ቢሆን የሚያጥረንን የነጻነት አየር እውነት እንድትጋፈጥ ያደርጉሃል። ለዚህ የነጻነት አየር ሲባል ጋዜጠኞች እና ሃሳባቸውን በመግለጽ ራሳቸውን የሚገድቡ ፖለቲከኞች በሽብርተኝነት ሲከሰሱ እና ሲታሰሩ ሃሳባቸውን እና የፖለቲካ አቋማቸውን ደገፍነውም አልደገፍነውም ሊከነክነን ይገባል።
ይህ የነጻነት አየር ከህገ መንግስቱ የሚመነጭ ነው፤ በዚህ ነጻነት አየር ላይ የሚጨመር የጥርጣሬ እና የፍርሃት ጭስ ህገመንግስታዊ ስር አቱን ቀስ በቀስ የሚሸረሽር መጥፎ አዝማሚያ ነው። "የኢትዮጵያን ህገመንግስታዊ ስርአት በጸና መሰረት ላይ ማቆም" ከፈለግን ለሁሉም አንቀጾቹ እኩል ተቆርቋሪነት ልናሳይ ይገባል።
በእኔ እምነት በመለስ ስርአት ውስጥ ከተበረከቱልን መልካም ነገሮች መካከል በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ውስጥ የተካተቱ የሰብ አዊ መብቶች ዝርዝር አንዱ ነው፤ ወደ እርግጠኝነት በተቃረበ ስሜት ማለት የምችለው ነገር ቢኖር፣ ኢህአዴግ አሁን የኢትዮጵያን ህገ መንግስት እንደገና ለመጻፍ እድል ቢሰጠው በተመሳሳይ መንገድ መብቶችን ይዘረዝራል ብዬ አላስብም፤ በተለይም፣ የመብቶችን አተረጓጎም በ አለም አቀፍ የ ሰብ አዊ መብት ሰነዶች መሰረት መሆን አለበት ይላል ብዬ አልጠብቅም። እንደማስበው ከሆነ ይህ ህገመንግስታዊ አቀራረብ፣ የኢትዮጵያን ዳኞች በህገ መንግስቱ ውስጥ የተካተቱ መብቶችን በ አለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ትር ጓሜ መሰረት እንዲተረጉሙ እድሉን ይሰጣቸዋል። ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚያጣብቡ የወንጀል ክሶች በተነሱ ቁጥር ዳኞቹ በወንጀል ህጉ አንቀጽ ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉ ከሆነ ፍርድ ቤቶች ከአስፈጻሚው አካል ነጻ ቢሆኑ እንኳን ነጻ መልቀቁ ቀርቶ ከባድ ቅጣት ከመወሰን ወደ ኋላ አይሉም። እስካሁን እያየነው ያለነው ይህንኑ ይመስላል።
አንዳንድ ሰዎች "ፍርድቤት ነጻ አይደለም ባስፈጻሚው ቁጥጥር ውስጥ ነው" ብዬ ለመናገር የማልደፍርበት ምክንያት ሊገርማቸው ይችላል። ምክንያቴ ግን ግልጽ ነው፤ የእስክንድር ነጋን ክስ የመረመረው ዳኛ ውሳኔውን የሰጠው የቀረበለትን ማስረጃ መርምሮ ይሁን ከአስፈጻሚው ትእዛዝ ተቀብሎ እራሱ ያውቃል።(ይህን ያነበቡ አንዳንድ ሰዎች "አሃ አንተ የፍርድ ቤት ነጻነትን ትእዛዝ በመቀበል እና ባለመቀበል ነው ማለት ነው የምትተረጉመው?" ሊሉኝ ይችላሉ።አይደለም!) ትእዛዝ ሳይቀበል በመሰለው እየሰራ ቢሆንና እኔ በሽህዎች ኪሎሜትሮች ርቄ ተቀምጨ ትእዛዝ እንደሚቀበል እርግጠኛ ብሆን ማን ነው የተሳሳተው? ይህንን የማደርገው የተከሰሰበትን አንቀጽ ፣ የቀረበበትን ማስረጃ፣ ያቀረበውን መከላከያ ሳላይ ለማወቅም ሳልፈልግ ከሆነ እንዴት አድርጌ ትክክል መሆን እችላለሁ? እንደዛ የማደርግ ከሆነማ የተከሰሰበትን አንቀጽ፣ የቀረበበትን ማስረጃ፣ ያቀረበውን መከላከያ ቢያውቁም ባያውቁም፣ ውሳኔው በህገ መንግስቱ ውስጥ የተካተተውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ይጥሳል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ቢያውቁም ባያውቁም፣ የሚወዱት እና የሚደግፉት መንግስት የሚደግፈው ውሳኔ ስለሆነ ብቻ እስክንድር ነጋ ለ አስራ ስምንት አመታት በእስር ቤት ውስጥ በመቆየት "ለማህበረሰብ ጎጂ የሆነው ጸባዩ ታርሞ"፣ "ለህብረተሰብ እንደገና ጠቃሚ ሰው" ሆኖ መውጣት አለበት የሚሉትን ሰዎች መምሰሌ ነው። ለዛም ነው አብዛኛው ክርክር በህገመንግስት መብቶች መከበር እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ዙሪያ እንዲሆን የምፈልገው። ለዛም ነው ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር የመጻረር ባህሪ ያላቸው የወንጀል ክሶችን የሚያዩ ዳኞች አይናቸውን ጨፍነው ውሳኔ የሚሰጡ ናቸው ብዬ ለመከራከር የሚከብደኝ።
አንድ ቀን መንግስት እርግጠኛ ሆኖ ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው የሽብርተኝነት ክስ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በጥልቅ የህግ ትንታኔ ውድቅ ያደረገ ጊዜ፣ ከማንም የማያንስ ህጋችን ከማንም በማያንስ መንገድ በተተረጎመ ጊዜ፣ ያኔ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለን እምነት ከፍ ይላል። በፍርድ ቤቶቻችን ላይ ያለን እምነት ከፍ ባለ ጊዜ፣ ህግን እና ህግን ብቻ መሰረት አድርገው እንደሚወስኑ ባወቅን ጊዜ፣ በፍርድ ቤት የተፈረደበትን ሰው "ጋዜጠኛ እኮ ነው"፤ "መብቱን እኮ ነው የተጠቀመው" ብለን የምንጮኸውን ጭሆት እንቀንሳለን። አሁን ግን እዚያ ጊዜ ላይ አይደለንም፤ የክስም የይቅርታም አጠቃቀም በፍትህ ስርአታችን ሙሉ እምነት እንዲኖረን አያደርገንም።
ከሁሉም ቀላል የሆነው መንገድ ግን ቆይተን ትዝብት ላይ ከምንወድቅ፣ እነዚህ አይነት ክሶችን አስቀድሞ አለመጀመር ነው፤ በእርግጥ ይቅርታም ቢሆን ይወጣል ብለን ካልጠበቅንበት ማጥ ውስጥ አውጥቶ አማረም ከፋም እንደገና ደህና እንድንመስል ያደረገን መልካም ነገር በመሆኑ እወደዋለሁ፤ በድህረ ዘጠና ሰባት የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስራት ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር ሳወራ በተመሰረተባቸው ክስ ምክንያት ሞት ሊፈረድባቸው እንደሚችል ሲጠቁመኝ የተሰማኝ ስሜት እና የሰጠሁት አስተያየት እስካሁን አይረሳኝም። "ያ የሚሆን ከሆነ ኢትዮጵያ አገሬ አይደለችም፤"ነበር ያልኩት በከፍተኛ ብስጭት እና ስሜት። የሆነውን ሁላችንም እናውቃለን፤ ሚሊኒየም ከመከበሩ በፊት የታሰሩት ሰዎች በይቅርታ ሲፈቱ መጀመሪያም መታሰር አልነበረባቸውም ብሎ የሚያምንም ሰው ቢሆን ደስ ተሰኝቷል፤
ከዚያ በኋላ በግለሰብ ደረጃ ሌላ ህግ ተኮር ብስጭት የደረሰብኝ የ ብርቱካን ሚዴቅሳ ይቅርታ ተነስቶ ወደ እስር ቤት ስትመለስ ነው፤ እስከ አሁንም ድረስ ሳስበው እውነት አይመስለኝም፤ "ሌላ አገር ሄደሽ ይቅርታ አልጠየኩም ብለሽ ስለተናገርሽ ያገኘሽው ይቅርታ ተጭበርብሮ የተገኘ ስለሆነ፣ ይህም በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ዋጋ ስለሌለው ተመልሰሽ ወደ እስር ቤት ትገቢያለሽ" ነበር የመንግስት ክርክር፤ ይቅርታ አድርጉልኝና ይህንን ክርክር በህይወቴ ከሰማኋቸው አስቂኝ እና እጅግ አበሳጭ የህግ ክርክሮች እንደ አንዱ አድርጌ እቆጥረዋለሁ። ለምን ያላችሁኝ እንደሆነ ስዊድን አገር ሄዳ ተናገረችው የተባለ ነገርን የሰማ መንግስት አዲስ ነገር ላይ የጻፈችውን ደብዳቤ ማንበብ አልቻለም። ያም ሆኖ ይቅርታን እወደዋለሁ፤ በስህተት ተመልሳ ታስራ በይቅርታ ስትፈታም ብዙዎቻችን ደስ ብሎናል።
በቅርቡ ደግሞ ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ይቅርታ ጠይቀው ሲፈቱ እንደ መልካም ነገር ተቀብለነዋል። ያም ቢሆን ግን ከነሱ ይልቅ የሚያሳስቡን ነገሮች አሉ፤ ምንም እንኳን የእስክንድር ነጋን ክስ እና የክስ ሂደት በቅርበት ባልከታተልም፣ በ አብይ እና በመስፍን ላይ ከተወሰነው የስምንት አመት ፍርድ አንጻር ስመለከተው (አድርገውታል የሚባለውን ነገር ስለምረዳ) መብትን ከመጠቀም አልፎ ለዚህ ቅጣት የሚያበቃ ከባድ ወንጀል ተደርጎ መወሰድ ያለበት ስራ ሰርቷል ብዬ አላምንም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እሱና መሰሎቹ ለህብረተሰብ ጎጅ ሆነው በመወሰድ በማረሚያ ቤት ውስጥ ላያሌ አመታት መቀመጥ የለባቸውም። ይህ ታሪክን የማበላሸት ተግባር ነው፤ አብሮህ ዘመን የሚጋራን ሰው በግድ ዝም ማሰኘት ልትችል ትችላለህ፤ ነገር ግን ከህሌናው ሚዛን አታመልጥም፤ ከታሪክ ተወቃሽነትም አትድንም። ይህን ጽሁፍ የጻፍኩት እስክንድር ነጋ እና መሰሎቹ ተፈትተው እንደኛ የነጻነትን አየር እየተነፈሱ በሚጽፉት ጽሁፍ እና በሚያቀርቡት ሃሳብ የሚፈልግ እንዲወዳቸው፣ የሚፈልግ እንዲያጥላላቸው እድል የሚያገኙበትን ቀን እየናፈቅኩ ነው።