Thursday 9 August 2012

መጠየቅ አይከፋም


ዛሬ ስለተደራጁ እና ሃሳባቸውን ስላደራጁ ሰዎች እየጻፍኩ አስባለሁ። አንተ የተማሩ ፣ የተመራመሩ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ ምእራባውያን ወዘተ ልትላቸው ትችላለህ። እኔ ደግሞ የተደራጁ እና ሃሳባቸውን ያደራጁ እላቸዋለሁ። ደበበ ሰይፉ በ 1966  “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” የሚለውን ድንቅ ግጥም ሲጽፍ(ደብዳቤው በወቅቱ በገጠር ስለነበረው ርሃብ በከተማ ላለው ማንነቱ ነው የተጻፈው)መግቢያው አካባቢ እንዲህ ይላል።  ሁለት ስንኝ ልዋሰው።

ይልቁንም ያይኔን እውነት፣ ለልቤ ያጫወትኩት ቢመስለኝ
ለራሴ የጻፍኩትን ደብዳቤ፣ ላንተ መላኩ አሰኘኝ።

ታዲያ እኔ እየጻፍኩ እንዳሰብኩት እናንተ ደግሞ እያነበባችሁ አስቡ። ያ ነው ለራስ የተጻፉ ደብዳቤዎችን የማጋራት አላማ።

ከተደራጁ እና ሃሳባቸውን ካደራጁ ሰዎች የምናስተውላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የተደራጁ ሰዎች ባደራጃቸው ሃሳብ ዙሪያ አስተሳሰባቸው ይቃኛል፤ በህብረት ሲዘምሩ ለራሳቸው ጆሮ ግሩም ዜማ ይሰማቸዋል። ለማንጎራጎር ስትሞክር የራስህ ድምጽ ለሌላው ሰው ከሚሰማው የተሻለ ሆኖ እንደሚሰማህ ሁሉ የተደራጁ ሰዎችም እንደዚያ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ጥሎባቸው ሰዎችን ይፈርጃሉ፡ ወዳጆች፣ ጠላቶች፣ ተለዋዋጮች፣ ተጨዋቾች፣ አጫዋቾች፣ አራጋቢዎች፣ ተመልካቾች ወዘተ ብለው። የፍረጃ አይነቶቹም ብዙ ናቸው፤ የሚገልጹት እውነታ እንዳለ መካድ ባይቻልም፣ የጭቆናና የማግለል መሳሪያ ሊሆኑ መቻላቸው ግን እሙን ነው። አብዮተኞች፣ የአብዮቱ ጠላቶች፣ ወንበዴዎች፣ ጸረ ህዝቦች፣ ቢሮክራቶች፣ መሃል ሰፋሪዎች፣ ሽብርተኞች፣ አክራሪዎች፣ የቀድሞው ስርአት ናፋቂዎች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ጥገኛ ባለ ሃብቶች፣ ልማታዊ ባለ ሃብቶች፣ ዲያስፖራ፣ አክራሪዎች.... እንደዘመኑ እና እንደባለ ዘመኖቹ ክፍፍሉ ይለያያል።  አንተ የትኛውን እንደሆንክ መጠየቅ አይከፋም።


ሃሳባቸውን ያደራጁ ሰዎችም ከተደራጁ ሰዎች ብዙ አይለዩም፤ ከፍ ባለ ቦታ ላይ ስለቆሙ፣  በዛ ያለ ነገር ያስተዉላሉ፤ ማን በማን ጉሮሮ ላይ ቁሞ ምን እንደሚበላ፤ ማን የማንን አንገት ቆልምሞ፣ ዞሮ አስተዛዛኝ እንደሚሆን ያስተውላሉ፣ ወይም ያስተዋሉ ይመስላቸዋል። የኔ ቢጤው ቀልቡ የመከረውን ሲቀባጥር፣ ሰብሰብ አድርገው አንድ ቅርጫት ውስጥ ያስቀምጡና ይፈርጁታል። ለምሳሌ አንዳንዶቹ የምታምነውን ፈጣሪ ስለማያምኑ፣ ስለ እምነትህ የሚጨነቁት ወይም የተጨነቁ የሚመስሉት ጠላት እንዳይበዛባቸው፣ ፊት እንዳትዞርባቸው ሊሆን ይችላል። አንተ እግዚያብሄር የፈቀደው ነው ትላለህ፤ እነሱ "እግዚያብሄር የፈቀደው ነው" ማለትህን የሂሳባቸው አካል አድርገው ስሌታቸውን ይሰራሉ።  “መጽሃፍ ቅዱስ ሰጡን፣ እኛ ወደ ሰማይ ስናይ እነሱ መሬታችንን ወሰዱ” የተባለው ለምን ይመስልሃል? እንደነሱ እንሁን እያልኩህ አይደለም፤ መኖራቸውን እንረዳ እንጅ። 


አንተ ሰው ነኝ ስትል ላንዳንዶቹ ቁጥር ነህ፣ ላንዳንዶቹ ጥቁር ለሌሎች ደግሞ ያ፤ ላንዳንዶቹ ሃይማኖትህን ነህ፤ ለሌሎቹ የሆነ ብሄር።  ስለ አንተ ነጻነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት የሚጨነቁ ከሚመስሉህ የሚበዙት ለእነዚህ ሁሉ ግድ የላቸውም፤ አንተ ትናንት ላይ እንድታፈጥ አድርገው፣ ዛሬህን ይሰርቁሃል፤ ዛሬ ላይ እንድታተኩር አድርገው ነገህን ይዘርፉሃል፤ ሰጡኝ ጸደቁብኝ ብለህ ስታመሰግን፣ እጥፍ ድርብ ያተርፉብሃል። ያንተ ፈገግታ የእውነት ነው፤ የነሱ ገግታ የማስመሰል። ያንተ ምስጋና የምር ነው፤ የነሱ ማመስገን የይስሙላ። ይህን ስልህ ፈገግታችንን የይስሙላ እናድርገው እያልኩህ አይደለም። በድህነት ላይ ክፋት ከጨመርክ፣ ህይወትህን የምድር ሲኦል ታደርጋታለህ። በችግር ላይ ቅንነት ማጣት  በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ማለት ነው። ከልብህ በቅንንነት በምታደርገው የሚገባህን ደስታ ከዚያው ታገኛለህ። 

አንተ የሰው ዘር መገኛ፣ ጥንታዊ የስልጥኔ አሻር ነኝ እያልክ በሌላ በኩል በእናንተ ሰፈር እና በእነ በቀለ ሰፈር መካከል ያለውን ልዩነት ስታወጣ ስታወርድ፣ እነሱ አንድ ላይ ጠቅልለው የአፍርካ ቀንድ ይሉሃል። እንደ ሱማሊያ ሃያ አመት ያለ መንግስት ብትኖር አንተ ግድ የሚልህ የጎሳ ልዩነቱ ሊሆን ይችላል፤ እነሱ ግን መንግስት እንድታቋቁም ከልባቸው የሚፈልጉት የባህር ወንበዴዎችህን እና አሸባሪዎችህን ለመቆጣጠር እንዲቻል ሊሆን ይችላል። ይሄ ምንም አይገርምም። ማንም የሚፈልገውን አቅዶ ለማግኘት መሞከሩ ጥሩ ነው። አንተም ታዲያ የምትፈልገውን ብታውቅ፣ የምታደርገውን ለመወሰን ይጠቅምሃል።የሚሆነው ሁሉ የሚሆነው ለምንድነው ብለህ ብትጠይቅ አይከፋም። አንተ ራስህን እና ሌሎችን የምታይበት መንገድ እና ሌሎች ራሳቸውን እና አንተን የሚያዩበት መንገድ ብቻ አይደለም ሊለያይ የሚችለው። የምታየው ወይም የምታየው የሚመስልህ  ሁሉ ያለ ነው ብለህ ከልብህ አትመን። ልክ አድማስን እንደመመልከት አድርገህ ውሰደው-ሰማይና ምድር ተነካክተው እንደሚታዩህ ማለት ነው። በእርግጥ የተነካካም ያልተነካካም ነገር የለም መሬትም ሰማይ ላይ ነው ያለችው። 

እዛው ከጎንህ ትናንሽ ድርጅቶች እና ሃሳባቸውን ያደራጁ ሰዎች አሉልህ።አይንህን ግለጥ ታያቸዋለህ፣ ዞር ዞር በል ታገኛቸዋለህ።አንተ ትናገራለህ እንጅ አታስተውልም፤ እነሱ ግን የሚናገሩህን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በወሬ ያደነዝዙሃል፣ በስሜት ልተወራጭ ትችላለህ እነሱ በስሜት እየተወራጩም ያስባሉ፣ ቀጥሎ  ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያወጡ ያወርዳሉ።
እንደ እኔ እና እንደ አንተ የሚሰማቸውን ስሜት እና የሚፈልጉትን ፍላጎት መነሻ ይዘው፣ ባነበቧቸው እና ባነበነቧቸው መጽሃፍት እና ስብከቶች መሰረት አደራጅተው ይዘምቱብሃል። ታዲያ የኔ ቢጤው አነጣጥሮ ተኳሽ ነኝ ሲመስልህ፣ ወይ ተተኳሽ ጥይት አልያም ኢላማ  ትሆናለህ።የምትተኮሰው ወደምትፈልገው እና ወደሚያስፈልግህ አቅጣጫ ከሆነ ጥሩ ነው።  አንዳንዴ ግን የምትፈልገው እንዲያስፈልግህ አድርገው ሰለሚቀርጹህ፣ እንደምትፈልገው እንጅ ለምን እንደምትፈልገው ላታውቅ ትችላለህ። በዚህም የተነሳ በገዛ አገርህ እና አሃጉርህ ባይተዋር ትሆናለህ።

አንተ ግን  በነቃህ ጊዜ፣ የሚደረገው ነገር በገባህ ጊዜ ስህተትን በስህተት ለማረም እሳትን በእሳት ለማጥፋት አትሞክር። መልካም ህልም ካለህ ለህልሞችህ መርሆች ተገዛ። ስህተትንም በስህተት ለማረም በመሞከር ስህተት አታብዛ።

No comments:

Post a Comment