Wednesday 1 August 2012

የህልሞች ውድድር


በዚህ የሃሳብ እጥረት እስር ቤት ውስጥ ካቅም በታች እያሰብን ስንኖር፣ የምናየው ያለውን ሳይሆን የምንፈልገውን ሲሆን፣ ኑሮአችን ይጠበኛል፤ አየራችን ያፍነኛል፤ አሻግሬ ማየት እሻለሁ፤ በጥሩ ህልም እራሴን ላረጋጋው እሞክራለሁ። በልባችን የቀበርነው የዝንጋኤ መጠን በጣም ያሳስበኛል፤ አስተሳሰባችን የሚመሰርትበት መሰረት ምን እንደሆነ እንኳን ለማወቅ ግራ ያጋባኛል። እኔ ግን ምኑ ነኝ ብዬ እጠይቃለሁ። ሜዳው ነኝ ወይስ ኳሱ?  ተጫዋቹ ነኝ ወይስ ተጠባባቂው? አሰልጣኙ ነኝ ወይስ  ዳኛው? ተመልካቹ ነኝ ወይስ ኳስ አቀባዩ?  እኔ ግን ማን ነኝ?

ሁሉንም ትቼ  ውስጤን ስፈትሽ ብዙ ያረጁ ሃሳቦች አገኛለሁ፤ ታዲያ ይህ በራሴ እና በመሰሎቼ ላይ ላይ የከፈትኩት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው። እስቲ ስለማያከራክሩ ነገሮች እናስብ፤ አገር ማለት እኔ አይደለሁም፤ አንተም አይደለህም፤ ታሪክንም ተማርከው እንጅ አልሰራኸውም፤ የቀደመውን ትናንትም ተማርከው እንጅ አልኖርከውም። ከማንነትህ የበዛውን ሆንከው እንጅ አልመረጥከውም።

ታዲያ እንዲህ ይሁን እንዲያ ይሁን ስንባባል፣ ይህ መንገድ ነው የሚሻለው ወይስ ያ መንገድ ነው የሚሻለው ብለን ስንሟገት ፣ በመሰርቱ ምን ማለት ነው? የሚያስጨንቀንስ ምንድነው? መቸም እድሜ ልክ እንኖራለን ብለን እንደማናስብ እርግጥ ነው። የግል ህይወታችን በጊዜ ገደብ የታሰረ ነውና፣ ከእስር ቤት የምናመልጠው በቀጣይ ትውልድ በኩል ካልሆነ በቀር በአካል አይሆንልንም፤ የፈለገውን ያህል ብንሮጥ መድከማችን፣ መውደቃችንም አይቀርም።

ታዲያ ስለ አገር ስናወራ ዋናው ነጥብ እኔ ወይም አንተ አይደለንም፤ ውድድሩም በእኔ እና በአንተ መካከል አይደለም። ውድድሩ የህልሞች ውድድር ነው።

የምታልማትን አገር ንገርኝ፤ የማልማትን አገር እነግርሃለሁ፤ የረጅም ርቀት የህልም ቅብብል እንደሚኖረን አስበን እንነሳ፤ የዛሬ ፵ አመት ወይም ፶ አመት ማሳካት የምንፈልገው ህልማችን የዛሬ ድርጊታችንን ይወስነው፤ በተሻለው ህልም ዙሪያ የበዛዉን ሰው ለማሰለፍ ጠንክረን በትግእስት እንስራ፤ ያንን ለማድረግ ታሪክን በታሪክነቱ  እንደምንፈልገው ሳይሆን እንደሆነው እንመርምረው፤ መጭውንም ጊዜ አቅማችንን አሰባስበን ለመጭው ትውልድ የምናስረክበው ትልቅ ህልም እናልምበት፤ እንተግብርበት።

እኔ ሳልኖርም ለሚኖር ህልም እንድሰራ እፈልጋለሁ፤ አንተም አንተ ሳትኖር ለሚኖር ህልም ጠንክረህ ስራ። ስለ አገር ስታልም ግን እኔንም አስበኝ፤ እኔም አንተን አስብሃለሁ። አውቃለሁ ታሪካችን በጣም ጥልቅ ነው፤ ውጣ ውረዳችንም የበዛ፣ በሃሳብ መለያየታችንም የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን ህልሞቻችን ቢለያዩም አቅጣጫቸው አንድ ይሁን፤ አለበለዚያ ግን ደባሎች እንመስላለን፤ አብረን የኖርነው ኑሮ ቀልድ ይሆናል። የተጋራነው እጣ ፈንታም እንዳልተጋራነው ይመስላል። ብዙዎች አሁን ከሚያደርጉት የተለየ ነገር ማድረግ ላይጠበቅባቸው ይችላል። ነገር ግን የምናደርገው ነገር ሁሉ ለራሳችን፣ ለህዛባችን እና ለአገራችን ካለን ህልም ጋር ይተሳሰር። ያኔ ባግባቡ ማቀድ እና መተግበር እንችላለን፤ እኛ ብናመልጥ እንኳን ህልማችን ይቀጥላል። ይህን ሁሉ ማለት ለምን አስፈለገ? ማንም ሰው ስለ አገሩ ሲያወራ ወይም ሲሰራ ስለራሱ ሊመስለው አይገባም። "ገዢም" ቢሆን ዛሬ በማስፈራራት ሰዎችን ዝም ማሰኘት ቢችል፣ ታሪክን ዝም ማሰኘት እንደማይችል ሊያውቅ ይገባል። ለአገሩ ያለው ህልም ከሱ ካልዘለለ፣ ወይም የራሱን ፍላጎት ብቻ እያሰበ ከተለመው ርቆ ሊሄድለት አይችለም።ሁሉም በጊዜው ተገዢዎቹን ዝም አሰኝቷል፤ በግድም በውድም አስጨብጭቧል። ጊዜው ሲያልፍ ግን እራፊ ጨርቅ የሚጥልበት እንኳን የለም።  ዜጋም ቢሆን በመርህ ካልተመራ፣ ያለ ህልም ከኖረ የስብከት ሰለባ የጭቆና መሳሪያ ከመሆን አይድንም። ለተስፈኛ ነገ ጥሩ ጓደኛው ነው፤ ያልተጨበጠ ቢመስልም፣ እኖናራለን ብለን ነው እና የምንኖረው፣ መንገዱም ረጅም ውጣ ውረዱም ውስብስብ ነውና የህልሞች ውድድር ይፋፋም።  ይችን ግጥሜን በጣም እወዳታለሁ፤ ህልማችሁን አስተካክሉ የሚል መልእክት ያላት ይመስለኛል። ተጋበዙልኝ።

ስለ እኔ ስል እኔ ስለ እኔ አትበሉ
ስለ እናንተ አይደለም መጭው ዘመን ሁሉ
መሻገሩ አይቀርም ቢረዝምም ቢበዛም
ይከራያል እንጅ አገር አይገዛም።


No comments:

Post a Comment