Friday 17 August 2012

ምናባዊ ክርክር


ይልቁንም ያይኔን እውነት፣ ለልቤ ያጫወትኩት ቢመስለኝ
ለራሴ የጻፍኩትን ደብዳቤ፣ ላንተ መላኩ አሰኘኝ።
                                                               ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ, ደበበ ሰይፉ, 1966
ምናባዊ ክርክር
ዲሞክራሲ ተኳኩላ ወደ ኢትዮጵያውያን ሄደች- ለሙከራ፤ ብዙዎች አላወቋትም።ይህች ፍቅር የሌላት፣ ክርክር የምታበዛ፣ ባህላችንን የማታከብር፣ በሰው ህመም የምትስቅ፣ በሰው ሞት የምትደንስ፣ ይሉኝታ የሌላት፣ የምንናፍቃት ዲሞክራሲ ወይም የሷ መልእክተኛ ልትሆን አትችልም” ብለው አመሳቀሏት።

 አንዳንዶቹ ግን አውቀዋታል፤ አይተው ግን እንዳላዩ መሆን ፈልገዋል።ይህች ባህላችንን ያልጠበቀች ጋጠ ወጥ ስለሆነች በኛ መካከል ምንም ቦታ የላትም” ብለው እያጥላሏት ነው። ሌሎች ደግሞ እሷ እንደሆነች ቢያውቁም፣ኢትዮጵያዊ መልክ ይዛ ካልመጣች፣ እንዳለ በምእራባዊ ልብስ አጊጣ፣ ተገላልጣ፣ እየጮኸች፣ እያወራች ልትገባ አትችልም” ብለው እየተቃወሟት ነው። 

አንዳንዶች ግንምንም ቢሆን ቦታ ሊሰጣት ይገባል፣ ጉልበተኞችን ማክበር፣ ባለጸጎችን ማክበር፣ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ማለት፣ ገና ለገና ባህላችን ነው ተብሎ እንዴት እንታፈን? እንዴት እንገለል?” እያሉ መጮሃቸውን ቀጥለዋል። ከዛም አልፈው  “ሲጀምር ይህ ባህል የምትሉት የጭቆና መሳሪያ እየሆነ እያገለገለ ስለሆነ መፍረስ አለበት” በማለት በቀጥታ ባይሟገቱም በተዘዋዋሪ ለመታገል እየሞከሩ ነው። ደግሞ ሌሎች አሉ፤እስቲ ቀስ በሉ፤ ሁሉንም ቀስ ብለን ማሳካት እንችላለን፤ ነገሮችን በእርጋታ እና በጥንቃቄ እናድርጋቸው፤ ያልሰራናቸውን የቤት ስራዎች ስለፈለግን ብቻ ከሚጠይቀው ጊዜ በፊት ማጠናቀቅ አንችልም፤ ስለፈለግን ብቻ በረን በሰላም እና በብልጽግና ሜዳ ላይ ማረፍ አንችልም። ህዝባችን ህዝባችን ነውና አፈራችንን አራግፈን አፈር ነህ ልንለው አንችልም። የገባን ነገር ካለ እናስረዳው፤ ከሁሉም በፊት ግን በንቀት ሳይሆን በት ህትና እንረዳው፤ ስሜታችንን በአመክንዮ ለማስደገፍ በምናደርገው ጥረት ጊዜአችንን አናባክን፤”  በማለት በመቅለስለስ ይናገራሉ።

“ምንድነው መለማመጥ?” ሌሎቹ የመልሳሉ።የምትቀሰቅሰው የተኛን ሰው ነው እንጅ አውቆ የተኛ የመሰለን አይደለም፤ የምታስተምረው የማይውቅን ሰው ነው እንጅ አውቆ እውቀቱን በስሜት እና በጠባብነት ይጠቅመኛል ለሚለው አላማ የሚያውለውን ሰው አይደለም። ሃዘኔታ እና ርህራሄ የሚያስፈልገው ደካማው ነው፤ ጥንካሬውን መቆጣጠር አቅቶት ደካሞቹን የሚጨፈልቀው አይደለም፤ብለው በጭሆት ይመልሳሉ።

ተቃራኒው ደግሞ ይከተላል፤እውነት አላችሁ፤ እውነት ግን እናንተ ብቻ አይደለም፤ ልትበሳጩ ትችላላችሁ፣ የሚሰሩ ስህተቶች ሊያሳዝኗችሁ ይችላሉ፤ ነገር ግን ያሳዛኞቻችሁን መሳሪያዎች ልትጠቀሙ አትችሉም። አሳዛኞቻችሁ ጥላቻ ስለተጠቀሙ እናንተ ጥላቻ ልትጠቀሙ አትችሉም፤ አሳዛኞቻችሁ መከፋፈል ስለተጠቀሙ እናንተ መከፋፈል  ልትጠቀሙ አትችሉም። እነሱ ሃያ አራት ሰአት ቢያዎሩ ሃያ አራት ሰአት ችላ ሊባሉ ይችላሉ፤ እናንተ ግን ባገኛችሁት ትንሽ እድል እንደ አሳዳጆቻችሁ ከሆናችሁ ፊት የሚዞርባችሁ ይበዛል።”

መሃል ገብቼ የሆነ ነገር ማለት ፈለኩ፤ ተከራከሩ ድንጋይ ግን አትወራወሩ፤ በሃሳብ ተቧቀሱ ጥይት አለመታኮሳችሁን ግን እንደ ትልቅ ድል ውሰዱት።ካልወደድከኝ አትኖራትም፤ከናቅከኝ አታድራትም” ያባቶቻችን ጨዋታ ነው፤ በቃ በሃሳብ ስለተለያየን፣ ከባህላችን ውጭ የሆነ ነገር ሰለተነጋገርን ኢትዮጵያ አለቀላት ልንል አይገባም፤ ኢትዮጵያ በሽዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በጅማላ ሲገደሉባትም አላለቀላትም፤ እናቶች ለተገደሉ ልጆቻቸው ያላቸውን እንባ አፍነው የጥይት ዋጋ ሲከፍሉም አላለቀላትም፤ አንድ እናት አራት ልጆቿን ምንነቱ ለማይገባት የርእዮተ አለም ልዩነት በአንድ ጀንበር ስታጣም አላለቀላትም፤ ሚሊዎኖች ሆነን በርሃብ ስናልቅ፣ መንግስቶቻችን ችላ ሲሉንም አላለቀላትም። ይህን የምለው አንዳንድ ሰዎች የሚሉትን በቅንነት ከልባቸው እንደሚሉ በመረዳት ነው። ከዚያ ውጭ ግን አውቆ የተኛን ለመቀስቀስ አልፈልግም፤ አልተኛማ።

No comments:

Post a Comment