Wednesday, 10 April 2013

ማንነት ያልተበደርነው እዳ



ሰዎች የሚያሳዝናቸውን ነገሮች ይመርጣሉ?  ሰዎች የሚያስደነግጣቸውን ነገር ይመርጣሉ? ሰዎች የሚያስከፋቸውን ነገር ይመርጣሉ?  አላውቅም! እኔ ግን ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቀሉ ስለተባሉት ሰዎች ከሰማሁ ወዲህ፣ አዝኛለሁ፣ ለጉዳዩም ብዙ ትኩረት ሰጥቻለሁ። በእርግጥ ምንድነው የሆነው?  ምን ያህል ሰዎች ናቸው የተፈናቀሉት? በምን አይነት ሁኔታ ነው የተፈናቀሉት?  በመኪና አደጋ ሞቱ የሚባሉት ሰዎች ነገር እውነት ነው?  ድርጊቱ የተደረገብት ዝርዝር ምክንያት፣ እና የተደረገበት አግባብ ምንድነው? ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጥያቄዎች ነበሩን፤ የምናገኘው በጣም ጥቂት መልሶችን ነበር።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛ አለ? እያልኩ ሁሉ ራሴን መጠየቅ ጀምሬ ነበር። አዲስ አድማሶች፣ መጀመሪያውንም ቢሆን ይህን ጉዳይ ለህዝብ ትኩረት ያበቁት እነሱ ናቸው፣ አሁን ደግሞ ስፍራው ድረስ በመሄድ እንዲህ አንጀት የሚበላ ግን ስለጉዳዩ እንድናስብ የሚያስችል ጽሁፍ አቀረቡልን። እጅግ ምስጋና ይገባቸዋል። ለጽሁፉ አዘጋጅ ደግሞ የተለየ ምስጋና።

ጽሁፍን ያነበብኩት በከፍተኛ ሃዘን ውስጥ ሆኜ ነበር። ራሴን በተፈናቃዮቹ ቦታ አድርጎ ለማሰብ አይጠበቅብኝም ነበር። ምክንያቱም እኔ ራሴ ተፈናቃዮቹን ነኝ።  እነዚህ ሰዎች ናቸው የተባሉትን ሁሉ ነኝ። ይህን የምለውም በከፍተኛ ሃዘን ነው። ጎጃሜ ናቸው ብለው ካሳደዷቸው፣ ጎጃሜ ነኝ። አማራ ናቸው ብለው ካሳደዷቸው፣ አማራ ነኝ፤ ደገኛ ብለው ካሳደዷቸው፣ ደገኛ ነኝ። ኢትዮጵያዊ ብለው ካሳደዷቸው፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ። በዚህም የተነሳ ይሆናል ህመሙ ዘልቆ የተሰማኝ።

አንድ የፌስ ቡክ ጓደኛዬ ስለነዚህ ሰዎች መፈናቀል ወሬ ሲደጋገምበት ጊዜ ይመስላል፣ "ቆይ እነዚህ ሰዎች አማራ ክልል የሰፈሩ ሽናሻዎች ቢሆኑና ቢፈናቀሉ ኖሮ ነገሩ እንደዚህ ይጋነን ነበር?" ብሎ ጠይቋል። ጥያቄው መልካም ነው። ትግራይ ኦን ላይን የተባለው ዌብ ሳይት ደግሞ በፊውዳል ኢትዮጵያ በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ በአማራ ገዥ መደቦች የተፈጸሙ ግፎችን የሚዘረዝር ጽሁፍ የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች ጉዳይ ዋና ርእስ በሆነበት ሰሞን አውጥቷል። ለነገሩ ጸሃፊው የግንቦት ሃያ ድል በአል እየተቃረበ ስለሆነ ነው ጽህፉን ያወጣሁት ያለው። አንዳንዶቻችን በልባችን ተወው ባክህ እንኳን ይችን የዝምብ ጠንጋራ እናውቃለን ብለን አልፈነዋል። ለጻፈበት ምክንያት ሳይሆን በጽሁፉ ውስጥ ላካተታቸው የታርክ እውነቶች እና የማህበረሰብ ትውስታዎች ስንል ግን ተገቢውን ክብር አልነፈግነውም።

በእውነት ግን ማንነት ያልተበደርነው እዳ ነው፤ ወደን በላያችን ያላወጣነው ሸክም። እውነተኛዋን ኢትዮጵያን ልተዋወቅ ወደ ጅማ ዩንቨርሲቲ ከማቅናቴ በፊት ነበር ለዚህ ምስክርነቴን የሰጠሁት።

ተወለድኩ
አባት አልመረጥኩም፣
እናት አልመረጥኩም፣
አገር አልመረጥኩም፣
ወገን አልመረጥኩም፣
ሆኜ ያገኘሁትን መርጬው አልሆንኩም። (7/2/96 E.C.)

ከላይ ያልኩትን ሁሉ የጻፍኩት የቤንሻንጉል ክልል ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ ወስኗል መባሉን ከመስማቴ በፊት ነው። ዛሬ ደግሞ ስለችግሩ ዘግበዋል ሲባሉ ያልሰማናቸው ጋዜጦች ስለመፍትሄው ውሳኔ ነግረውናል። እንደ አዲስ አድማስ ባይሆንም እነሱንም ቢሆን በመጠኑ እናመሰግናቸዋለን።  አንዳንድ ነገሮችን ማለት ወደድኩ።

አንድን የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል በሚጋራው የፖለቲካ፣ የዘር፣ የዜግነት፣ የብሄር፣ የባህል፣ የሃይማኖት ወይም የጾታ ማንነት መነሻ ማሳደድ(persecution) የሰብአዊነት ዝቅጠት ብቻ አይደለም። በ አለም ላይ አስከፊ ከሚባሉ ወንጀሎች አንዱ የሆነው በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸመ ወንጀል የመሆን ሁሉ እድል አለው።(see article 7 of the Rome Statute of the International Criminal Court) ይህ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ እንደኢትዮጵያ ባሉ የብዝሃነት ችግር በሌለባቸው አገሮች። ኦሮሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛቱ ወደር የሌለው ብሄር ነው። በ አማራ ክልል ውስጥ ግን አናሳ ብሄር ነው። አማራ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው ብዙ ብሄር ነው፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ግን አናሳ ብሄር ነው። ማንነት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ ቁማር ያችን አገር መውጫ የሌለው ጥፋት ውስጥ ነው የሚከታት። የቡድን እና የግለሰብን መብት በጋራ ለማክበር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ትክክለኛውን ሚዛን ማግኘት ከባድ ቢሆንም፣ ከእንደዚህ አይነት እብደቶች መታቀብ ካልተቻለ እጅግ እጅግ አሳሳቢ ነው።

ከ አምስት አመት በፊት የኬንያን ምርጫ ተከትሎ የሆነውን የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና የክልል ባለስልጣናት ቀረብ ብለው ሊያጤኑት እና ሊመረምሩት ይገባል። ዛሬ የኬንያ ፕሬዝዳንት ለመሆን የበቃው ሰው ምን አድርገሃል ተብሎ በምን ወንጀል እንደተከሰሰም ቀረብ ብለው ሊያጤኑት ይገባል። የኪራይ ሰብሳቢነት፣ እና የ አፈጻጸም ስ ህተት ቋንቋ ለእንደዚህ አይነት አስቀያሚ ተግባር በጣም ይጠበዋል፤ አይበቃውም።

በሌሎች አገራት በግጭት ጊዜ በደም ፍላት የሚደረግ ተግባር በኢትዮጵያ በ አማን አገር እየተደረገ ነው ሲባል የማይደነግጥ ሰው መኖር የለበትም። አንድ ሰው የገደለ፣ አንድ ሰው የሰረቀ፣ አንድ ሰው የሰደበ፣ አንድ ሰው የደበደበ ምን ያህል ይቀጣል?   የአንድ ሽህ ሶስት መቶ አርባ ስድስት ቤተሰብ ህይወት ያመሳቀለ ሰው ምን ያህል ይቀጣል?  ይህ የ አፈጻጸም ስ ህተት ተብሎ መታለፍ የለበትም።

ባለስልጣናቱ ይሏቸዋል የሚባሉ አንዳንድ ንግግሮች እውነት ከሆኑ፣ የቤንሻንጉል ክልል አንዳንድ ባለስልጣናት የክልሉ የብሄር ቁጥር ሚዛን እንዳይበረዝ በከፍተኛው እንደሚሰጉ ያመለክታል። ከሌላ ክልል የሚመጡ ማህበረሰቦች ቁጥር እየበዛ ከሄደ፣ በ ገንዘብ ያላቸው ጥንካሬ እየጨመረ ከሄደ፣ ወደ ስልጣኑም መምጣታቸው አይቀርም የሚል ስጋት እንዳለባቸው ያስታውቃል። ይሄን ስጋታቸውን ተገቢ ስጋት አድርገውም የቆጠሩት ይመስላል። በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ እጅግ በጣም አደገኛ የዘር ማጽዳት(ethnic cleansing) ጽንስ አለ። እነሱ ግን ይህንን ህግ እንደማስፈጸም አድርገው ነው ያሰቡት።

የሆነው ሆኖ ይህን በጣም አስቀያሚ ተግባር ከመፈጸም ለመከላከል ባይቻልም፣ ለማረም ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ማውቅ መልካም ሆኖ ታይቶኛል። የተፈጸሙ ነገሮችን ለማጣራት እና ለሌሎችም ሰዎች መማሪያ ይሆን ዘንድ እውነቱን ለህዝብ ለማሳወቅ ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጣ የ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ ሪፖርት ቢያደርግ ደግሞ እጅግ በጣም የተሻለ ይሆን ነበር።

አንድ ሎተሪ አዙሮ ኑሮውን ይገፋ የነበረ ሰው፣ አንድ ጉልበቱን ሽጦ የሚያርስ አርሶ አደር፣ ባለመረጠው የማንነት ሸክም እዳ ከፋይ ሲሆን ማየት ግን ከሁሉም በላይ ያማል።
አዎ፤ ማንነት ያልተበደርነው እዳ፣ ያልመረጥነው ሸክም ነው። አንድም ሰው ቢሆን በማንነቱ ምክንያት ጥቃት ደረሰበት ሲባል ሁሉም ሰው በሚችለው አቅሙ ሁሉ ያንን ነገር ስ ህተት መሆኑን ከመናገር እና ከማውገዝ መቆጠብ የለበትም። ዛሬ ሁላችንም በስማችን የምንጠራ፣ በትምህርት ደረጃችን፣ በግለሰብ ደረጃ በምናንጸባርቃቸው ደግነቶች፣ መልካም ንግ ግሮች፣ መጥፎ ተግባራት ወዘተ የምንታወቅ ልንሆን እንችላለን። አንድ ቀን አንዱ ተነስቶ አለኝ የምትለውንም ሆነ/አለኝ የማትለውን ማንነት አሸክሞ ሊያጠቃህ ቢጀምር ያኔ ከሰውነት ወርደህ የሆነ ቡድን አባል መሆን ብቻ ወንጀልህ ይሆናል። በሁለተኛው አለም ጦርነት ጊዜ አይሁዶች ላይ የሆነው ይሄው ነው፤ በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የሆነው ይሄው ነው። በቦስንያ ሙስሊሞች ላይ የሆነው ይሄው ነው። የዛሬ አምስት አመት ገደማ ኬንያውያን አንዳቸው በሌላቸው ላይ ያደረጉትም ይሄው ነው። ለኢትይጵያ ህዝብ ከእነዚህ  በ አንዳቸውም ላይ የተፈጸመው አንድ መቶኛ እንኳን ሲፈጸም ያኔ ቀፎው እንደተነካ ንብ ተነስተን ያንን ማረም አለብን።

ዝምታው፣ ቸልታው እንዳለ ሆኖ የተፈጸመው ነገር ያሳሰባቸው ሰዎች ደጋግመው ሲናገሩ፣ "ይህን የሚለው አማራ ስለሆነ ነው?" "ይህን የሚለው ጎጃሜ ስለሆነ ነው?" "ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲል አልነበረም እንዴ?" ወዘተ አይነት እንደቀልድም ቢሆን የሚነገር ሃሳብ መስማት በጣም ያማል። ይህን ነገር ተከትሎ በሚከሰት ጭሆትና የአቤቱታው አቀራረብ፣ "የአማራ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ይለምልም" የሚለው የብአዴን መፈክር እየተሳካ ይሄዳል ብለው እንደሚደሰቱ ወይም እንደሚሰጉ ሁኔታቸው የሚያሳብቅባቸው ሰዎች እንዳሉ ማወቅ ያቃጥላል።

የሆነው ሆኖ፣ በእርግጥ እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ መጡበት የሚመለሱ ከሆነ፣ ከደረሰባቸው ሰቆቃ አገግመው፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እንደገና በሰላም የሚኖሩበት መንገድ በሚገባ መመቻቸት ይኖርበታል።