ትናንትና ከዞን ናይኖች መካከል ሶስቱ ፍርድቤት ቀርበው ፖሊስ ሌላ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ ሁለት ሳምንት ገደማ እንደፈቀደ ሰምተናል። በጸረ ሽብርተኝነት ህጉ እያንዳንዱ የጊዜ ቀጠሮ ከሃያ ስምንት ቀን ማነስ የሌለበት ሆኖ ሳለ( አጠቃላይ የምርመራ ጊዜው ከ አራት ወር እስካልበለጠ ድረስ) አነስ ያለ የጊዜ ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት ጉዳዩ ተመልሶ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት መታየት በመጀመሩ ይሁን ወይም በዳኛው ስ ህተት ወይም ደግሞ ጉዳዩ ከቀሪዎቹ ተከሳሾች ጋር በሁለት ሳምንት በመለያየቱ ያንን ለማስተካከል ከመንግስት በተዘዋዋሪ በመጣ ትእዛዝ ለማወቅ አይቻልም። የሆነው ሆኖ ስለዚህ ጉዳይ ለመጻፍ ሳስብ አንዳንድ የፌስ ቡክ ወዳጆቼ ከተቃውሞ ሰልፉ ጋር በተያያዘ የታሰሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ይፈቱ የሚል ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነ ተረዳሁ። ዞን ናይኖች እንዲህ በብዙ ሰው ትኩረት ውስጥ ሆነው ሳለ እስካሁን ባለው ሂደት የታዩና የተሰሙ አንዳንድ ሁኔታዎችን ስናስብ፣ በተመሳሳይ የህዝብና የሚዲያ ትኩረት ውስጥ ያልገቡ በየቦታው ከተቃውሞ ሰልፉ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ለመብት ጥሰትና ለእንግልት ከዞን ናይኖችም በላይ የተጋለጡ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። ከዞን ናይኖች ጉዳይ ጋር እያዛመድን አንዳንድ ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን።
የታሰሩ የኦርሞ ተማሪዎች በተያዙ በ አርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ወይ?
በዞን ናይኖች ክስ ሂደት መንግስት በትክክል ከሰራቸው ነገሮች አንዱ በወንጀል ጠርጥሪያቸዋለሁ ብሎ ከያዛቸው በኋላ በ አርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ማቅረቡ ነበር። ፍርድ ቤት የመቅረባቸው አላማ የሆነው የተያዙበትን ምክንያት በቂነት የማረጋገጥና ከጠበቃና ከዘመድ ተለይተው እንግልት እንዳይደርስባቸው የማድረግ አላማ በሚገባ ተደርጓል ባይባልም፣ ፍርድ ቤት በጊዜው መቅረባቸው ባያስመሰግንም አያስወቅስም። ከተቃውሞ ሰልፉ በኋላ የተያዙ የኦሮሞ ተማሪዎች በእርግጥ የተያዙት በወንጀል ተጠርጥረው ከሆነ ተመሳሳይ በቶሎ ፍርድ ቤት የማቅረብ ተግባር መፈጸሙን አናውቅም።
ተማሪዎቹ ከተለያየ አይነት የእንግልት እና የማሰቃየት ተግባር ተጠብቀዋል ወይ?
የብዙዎቻችንን ትኩረት አግኝቶ የነበረው የዞን ናይኖች ጉዳይ ልጆቹን በ አርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት በማቅረብ ቢጀመርም፣ ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ከቤተሰብና ከጠበቃ ለይቶ በማቆየት የጊዜው መንግስት እንደዚህ ትኩረትን በሚስቡ እና ሰው ሁሉ በሚከታተላቸው ጉዳዮች እንኳን ለ አገሪቱ ህገ መንግስትና መብትን የሚደነግጉ ህጎች ያለውን ንቀት አሳይቷል። ይህ ሁኔታ ትኩረት ባገኘው የዞን ናይኖች ጉዳይ እንዲህ ያለው ተግባር ከተፈጸመ፣ በተለያዩ የ አገሪቱ ክፍሎች በብዛት ለእስራት በበቁትና ቁጥራቸው ተለይቶ በማይታወቅ ወጣቶች ላይ ምን ተደርጎ ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ከዞን ናይን ታሳሪዎች መካከል የተወሰኑት ፍርድ ቤት ቀርበው የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞብናል ሲሉ በተናገሩት ላይ ተመስርቶ የተደረገ የምርመራም ሆነ የማጣራት ተግባር አለመኖሩ የጊዜው መንግስት እንዲህ ያለውን አሳፋሪ ተግባር ለመከላከልም ሆነ ሲደርስ እርማት ለመውሰድ ተቃማዊም ሆነ የ አሰራር ዝግጁነቱ እንደሌለው ግልጽ አድርጎታል። እንዲህ ትኩረት በሳበ ጉዳይ ላይ እንዲህ ያለው ግዴለሽነትና ማን አለብኝነት ከተስተዋለ በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች በታሰሩ ተማሪዎች ላይ ይህን የመሳሰለው ነገር እንዳልተፈጸመ ምን ማረጋገጫ ይኖራል? አያያዛቸው ከዞን ናይኖች አያያዝ የባሰ እንደሚሆን ግን መገመት ይቻላል። በፖሊስ ይዞታ ውስጥ ሆኖ የሞተ ተማሪ እንዳለ ሁሉ ሰምተናል። ይህን ተከትሎ ምን ምርመራ ተደረገ? ምናልባትም ምንም። እንደ ሰብ አዊ መብት ኮሚሽን ያሉ ተቋማት ከውጭ የሰብ አዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመሟገት የ አገሪቱን ገጽታ ላለማበላሸት እየጣሩ እንደሆነ ነግረውናል። የቱሪዚም ቢሮ ናቸው እንዴ እነሱ?
አንዳንድ ሰዎች ተጠርጣሪዎች በቀጥታ ፍርድ ቤት እየቀረቡ የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞብናል፣ እንዲህ እና እንዲያ ያለው እንግልት ተደርጎብናል እያሉ እንኳን አንዳች ድንጋጤና ጭንቀት አይሰማቸውም። ለምን እንደሆነ አይገባኝም። በደርግ ጊዜ ያ ሁሉ የማሰቃየት ተግባር በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ሲፈጸም የወቅቱ ስርዓት በንጉሱ ጊዜ የወጡ ተጠርጣሪዎች በተያዙ በአርባ ስምንት ሰዓት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ ተገደው ቃላቸውን እንዳይሰጡ፣ ጠበቃ እንዲያገኛቸው ወዘተ የሚደነግጉ ህጎችን እንደማይጠቅም የፍ ትህ አተያይ ቆጥሮ ችላ ብሏቸው እንደነበረ ልንረሳው አይገባም። አሁንም በህገ መንግስቱ እና በሌሎች ህጎች ላይ የተቀመጡ የዜጎችን መብቶች በተመለከተ ከርዕዮተ አለማዊ ዝንባሌ የሚመነጭ የንቀት አተያይ በ አንዳንድ ሰዎች ዘንድ አስተውላለሁ። ስለ መብት የሚያወራ ሰው ስለ አገሪቱ መልካም ነገር ማውራት የማይፈልግ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩም አሉ። ይሄ ትክክል አይደለም። ስ ለ አገሩቱ መልካም መልካሙን ብቻ መርጦ ማውራት አገርን መውደድ አይደለም። ደርግም በጣም ለብዙ ዘመናት በሰሜን የነበረውን ጦርነት ከኢትዮጵያ ህዝብ አይንና ጆሮ ደብቆ እንደኖረ ልናስታውስ ይገባል። ርሃብንም የደበቅንበትና ሰው በጠኔ እንዲሞት የፈቀድንበት ታሪክ አለን። በቀይ ሽብርና ከዚያም በኋላ በ አገሪቱ ውስጥ የሆነውንና የተደረገውን ኢሰብዓዊ ድርጊት በሚገባ አውግዘን እንዳይደገም ለራሳችን ቃል ገብተን እየኖርን አይደለም ያለነው። ይሄ ደግሞ መሻሻሎች ቢኖሩም ከግፍ ቀለበት እንዳንወጣ አድርጎናል። የለመለመ መስክና የተንጣለለ አስፋልት እያሳዩ መመጻደቅ አገርን መውደድ አይደለም። የ አሜሪካ ጦር በኢራቅ አቡግራይብ እስር ቤት የፈጸመውን ግፍ ያጋለጡት እና ያራገቡት እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽና ያሉ የሰብ አዊ መብት ተሟጋቾች ናቸው። ተመሳሳይ ድርጅት የተቃውሞ ሰልፎቹን ተከትሎ እንዳወጣው ያለውን አይነት መግለጫ በትኩረት አይተን እርምጃ ብንወስድ የምንጠቅመው እኛ ነን። የምናሰቃየው፣ የምናዋክበው እና የምናንገላታው እንደ አሜሪካኖቹ እንኳን በሰው አገር ሄደን አይደለም። የገዛ ህዝባችንን ነው። ያንቀላፋ ህሊናችን ሊነቃ ይገባል። በየ እስር ቤቱ ያሉ የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመባቸውን ማሰቃየት፣ በደልና እንግልት ሊቆም ይገባል። ነጻነታቸውንም ማግኘት አለባቸው።